በሲዳማ ክልል የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርኃግብር ተከናወነ

ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርኃግብር ተከናወነ።
ዛሬ በጉዱማሌ በተጀመረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኘሮግራም ላይ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ኘሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ፣ የችግኝ ተከላ ኘሮግራም ያከናወኑ ሲሆን የከተማው የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
መርኃግብሩን ያስጀመሩት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ኘሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በዚህ ክረምት ወራት 128 ሺህ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ከ80 ሚሊየን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሀብት በክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ እንደሚሸፈን የተናገሩት ረዳት ኘሮፌሰር ፀጋዬ፣ ወጣቶች የበጎ ተግባር ተምሳሌት በመሆን ለሀዋሳ ከተማም ሆነ ለሀገር የበኩላችውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከንቲባው ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሁሉም ክፍለ ከተማ የሚከናወን መሆኑን ገልጸው፥ በመክፈቻው ስነስርዓትም በሀይቅ ዳር ክፍለ ከተማ፣ በባህል አዳራሽ፣ በጨፌና በገመጦ ቀበሌ በዝቅተኛ ኑሮ የሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖችን በመጎብኘት የቤት ጥገና ማስጀመሪያ አከናውነዋል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት ወ/ጻዲቅ ወጣቶች ህብረተሰቡን በመርዳት ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ የሚሆን ተግባር ለመፈጸም ችሎታም አቅምም እንዳላቸው ተናግረዋል።
ቤት የሚጠገንላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለተደረገላቸው ድጋፍ ማመስገናቸውን ከከተማ አስተዳሩ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።