በደሴ ከተማ እየደረሰ ያለው የመሬት መንሸራተት ችግር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተባለ

ነሐሴ21/2016(አዲስ ዋልታ) በአማራ ክልል ደሴ ከተማ እየደረሰ ያለው የመሬት መንሸራተት ችግር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተወካይ ማህተመ ኃይሌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ተወካዩ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል በደሴ ከተማ አስተደዳር በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ባጋጠመ ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ከ200 በላይ ወገኖች በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

የከተማ አስተደዳሩ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት በአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎችን ወደሌላ ስፍራ የማዘዋወር ስራ እየሰራ መሆኑን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ሕብረሰተቡን በማሳተፍ የጎርፍ ማፋሳሸ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም ችግሩ ከከተማ አስተደዳሩ አቅም በላይ እንደሆነ ነው የተመላከተው፡፡

ስለሆነም የሚመለከታቸው የክልል እና የፌደራል አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በከተማዋ እየደረሰ ላለው የመሬት መንሸራተት አደጋ ትኩረት በማድረግና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ህዝቡን ሊታደጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡