በግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ሁኔታ ቁጥጥር እንደሚካሄድ ባለሥልጣኑ ገለጸ

ነሐሴ 1/2014 (ዋልታ) የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ የቁጥጥር ሥራ በማካሄድ ከመመሪያ ውጪ ያልተገባ ክፍያ አስከፍለው የተገኙ ተቋማት ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።
የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ ተቋማት የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ ባለስልጣኑ ቁጥጥር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቁመዋል።
‹‹የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ ቁጥጥር ይካሄዳል፣ በመመሪያው መሠረት ያላግባብ ያስከፈሉ ካሉ ገንዘብ እንዲመልሱ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ ርምጃዎች ይወሰዳል›› ነው ያሉት።
በተደረገው አጭር ምልከታ 12 የግል ትምህርት ቤቶች ጭማሪን አስመልክቶ የወጣውን መመሪያ ጥሰው በመገኘታቸው ከመመሪያ ውጪ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለወላጅ መልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዙንም ተናግረዋል።
በመመሪያ አተገባበሩ ላይ የተለያዩ ጥቆማዎች እየደረሱ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ አንዳንድ ተቋማት የምዝገባ ክፍያ መጨመር፣ በዓይነት መጠየቅ እና የመሳሰሉ ያልተፈቀደ ክፍያ ጭማሪ እያደረጉ እንደሚገኙ ጥቆማ ደርሶናል፤ ወርደን እያስተካከልን እንገኛለን ብለዋል።
ለክትትል የሚላኩ ባለሙያዎች አቅጣጫ ተሰጥቶ እንደሚላኩ በመጠቆምም፤ ባለሙያዎች የተከፈለበትን ደረሰኝ ተመልክተው እንዲያረጋግጡ የሚያደርግ የመገምገሚያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።
ከባለሙያዎች አቅም ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ተቋማትን ለማየት በቅርንጫፍና በዋና መስሪያ ቤት ያሉ ባለሙያዎች በማሰማራት በሚገባ ለመገምገም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ከመመሪያው ውጪ ወርሃዊ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎችን አስከፍለው በተገኙ ተቋማት ላይ ርምጃ ይወሰዳል፣ ለሕዝብም ይፋ ይደረጋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ ሲያጠናቅቁ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት በተዘጋጀው ወጥ የመገምገሚያ ዝርዝር ሃሳብ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ተቋማት ላይ ምልከታ በማድረግ የማስተካከያ ርምጃ ይወሰዳል።
በአብዛኛው እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ምዝገባ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከነሐሴ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማትን በመዘዋወር የሚደረገው ምልከታ ያላግባብ ክፍያ የተቀበሉ የትምህርት ተቋማት ገንዘብ እንዲመልሱ ከማድረግ ጀምሮ አስተዳደራዊ ርምጃ የሚወሰድ ይሆናል።