በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ሃሳቦችን በመተግበር የተሻለ ውጤት ለማምጣት መታቀዱ ተገለጸ

ነሐሴ 1/2014 (ዋልታ) በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች ከማስፋት ባለፈ አዳዲስ ሃሳቦችን በመተግበር በ2014/15 የምርት ዘመን ከግብርናው የሚጠበቀውን ፍላጎት ለማሳካት መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
በ2013/2014 የምርት ዘመን በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤታማ አፈጻጸም በዘርፉ ላይ መነቃቃት እንዲፈጠር ማድረጉም ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴርና የክልል ግብርና ቢሮዎች የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2015 ዓ.ም ዕቅድ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን በዚህ ወቅት ዘርፉ ከኢንዱስትሪ፣ ከምግብና ከኤክስፖርት አኳያ ከፍተኛ ፍላጎት እንደሚቀርብበት ጠቅሰዋል፡፡
ግብርናው የእነዚህን ዘርፎች ፍላጎት እንዲመልስ በቂ ዕውቀት የተላበሰና ሙያውን የሚረዳ አመራር ይጠይቃል ብለዋል።
የግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ እስኪደረግበት ድረስ ፈተናዎች እንደማያጡት የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ፈተናዎችን የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያነሱት።
የ2013/2014 የምርት ዘመን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም ግብርናው መልከ ብዙ ፈተናዎችን ቢያሳልፍም የተሻሉና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው አፈጻጸሞች እንደታዩበት አንስተዋል።
በምርት ዘመኑ ከአጠቃላይ ወጪ ምርቶች ግኝት ግብርናው 72 በመቶ ሲሸፍን፣ በተለይም በቡና ኤክስፖርት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን አስታውሰዋል።
በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በስጋ ኤክስፖርት ከዕቅዱ አንጻር የተሻለ አፈጻጸም እንደነበር ገልፀው፤ በቀጣይ የአሰራር ስርዓትና የአመራር ሚናው ከተስተካከለ የተሻለ አፈጻጸም እንደሚኖር ገልጸዋል።
በዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት መኖሩን ጠቁመው የፌዴራልና ክልል አመራር ህዝብን አሰልፎ ሚናውን በአግባቡ መወጣቱ ስኬት ለማስመዝገብ አጋዥ መሆኑን በተግባር ማሳየት ተችሏልም ብለዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከገጠሟት ተግዳሮቶች አንፃር ሲመዘን ዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም እንደነበረው ገልፀዋል።
በመሆኑም በዓመቱ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በኤክስፖርትና ገቢን በማሳደግ ረገድ መልካም ውጤቶች እንደተገኙ አንስተዋል።
የሜካናይዜሽን እርሻን በሁሉም ክልሎች ማስጀመር የተቻለበት እና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አፈጻጸም ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ስሟ የተወሳበትን ውጤት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
በምርት ዘመኑ በመኸር ምርት ለመሰብሰብ ከታቀደው 374 ሚሊዮን ኩንታል 336 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመሰብሰብ የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት ተችሏል።
ይህን ስኬት ለማስቀጠል ከቴክኖሎጂ አቅርቦት እና ስራውን ከማሳለጥ አንጻር የ2014/2015 ምርት ዘመን ትልቅ የቤት ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት።
በእንስሳት ልማት ዘርፍም በዶሮ ልማት፣በዝርያ መሻሻልና ስጋ ልማት ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም ቀሪ ስራዎች ስለሚጠብቁን መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ነው ብለዋል።
የ2015 ዓ.ም ዕድቅ የተለጠጠ በመሆኑ ግቡን ለማሳካት ከየተቋማቱ ትልቅ ጥረት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ጠንካራ ጎኖችን ማስፋት ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ሃሳቦችን ወደተግባር በመቀየር የኢንዱስትሪዎችን የግብዓት እጥረት ማሟላት፣የወጪ ምርትን መጠን ማሳደግና የከተማ ግብርናን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህ ስኬት የፌዴራልና የክልል ተቋማት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎችም በቀጣይ የምርት ዘመን ለታቀዱ ግቦች ውጤታማነት አበክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አበራ ወርቁ ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፈው የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ልማት ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ክልሉ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የውጭ ገቢ ተኪ ምርቶችን በመጠንም በአይነትም መጨመርና ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አራት አንኳር ግቦችን ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል።
በምርት ዘመኑ በመኸር 205 ሚሊየን፣ በመስኖ 17 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱንና ለዚህ ይረዳ ዘንድ በግብዓት አቅርቦት ዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
የጋምቤላ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኩዌት ሉል በበኩላቸው ክልሉ በግብርና ዘርፍ ትልቅ አቅም እንዳለው ገልፀው፤ በቀጣይ ምርት ዘመን 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጸዋል።
ክልሉ ቀደም ሲል በቆላ ስንዴ የሸፈነው መሬት 100 ሄክታር ብቻ እንደነበር አስታውሰው በቀጣይ በ2 ሺህ 100 ሄከታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።