ቦርዱ ምርጫው በተያዘለት ቀነገደብ እንዲከናወን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

የካቲት 24/2013 (ዋልታ) – የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ምርጫው በተያዘለት ቀነገደብ እንዲከናወን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዕጩዎቸ ምዝገባ ሂደት ያለበት ሁኔታ፣ የቀረቡ አቤቱታዎችና የተሰጡ የመፍትሄ ሃሳቦች በተመለከተም የቦርዱ ሰብሳቢ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እጩዎቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ጥሪ የቀረበ ቢሆንም ፓርቲዎቹ የጊዜ ገደቡ እንዲራዘምላቸው ጠይቀዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ በሚካሄደው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተወዳዳሪ ዕጩዎች ምዝገባና የመራጮች ጉዳይን አስመልክቶ አራተኛውን ተከታታይ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ የምርጫ ምልክት የወሰዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችና የምርጫ ቦርድ አመራሮች ተገኝተዋል።
አሁን ባለው ሪፖርት 15 ፖርቲዎች እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውንና ከ2 ሺህ በላይ ዕጩዎች እንደተመዘገቡ የገለፁት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማለፍ ጊዜው እዲራዘም ሲደረግ የቆየ በመሆኑ ምዝገባው ሊራዘም እንደማይችል ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት ብልጽግና፣ ኢዜማ፣ ባልደራስ፣ አብን እና ሌሎችም ፓርቲዎች በእስከዛሬው የምርጫ ሂደት ታይተዋል ያሏቸውን ችግሮች አንስተዋል፡፡
ከተነሱት ችግሮች መካከል የአስፈፃሚ አካላት በቢሮ አለመገኘት እና የእጩዎች መታሰር የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የበጀት እጥረት መኖሩንም አንስተው መፍትሄ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመረጃ ማዕከል አሠራር፣ በዕጩዎች ምዝገባ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን መረጃ ለቦርዱ ለማድረስ እንዲረዳ ምርጫ ቦርድ “665” ነጻ የስልክ የመረጃ ማዕከል አዘጋጅቷል፤ ሁሉንም የምዝገባ ጉድለቶች መረጃ ለመስጠትና ለመቀበል የሚያስችል ነው ተብሏል።

(በሳራ ስዩም)