ቦትስዋና በመጠኑ በዓለም 3ኛ የሆነ የዳይመንድ ማዕድን አገኘች

ሰኔ 10/2013 (ዋልታ) – በአፍሪካ በዳይመንድ ምርት ቀዳሚ እንደሆነች የምትታወቀው ቦትስዋና በመጠኑ በዓለም 3ኛ የሆነውን የዳይመንድ ማዕድን ማግኘቷን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞክግዊትሲ ማሲሲ አስታወቁ፡፡

አዲስ የተገኘው የዳይመንድ ማዕድን ባለ 1 ሺህ 98 ካራት ጥራት ያለው እና በመጠኑ ከዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ መሆኑን የቦትስዋና የዳይመንድ ማዕድን ተቆጣጣሪ ተቋም ዳይሬክተር ሊይኔቴ አርምስትሮንግ ተናግረዋል፡፡

በመንግስትና ዴ ቢርስ በተባለ ዓለም አቀፍ የዳይመንድ ማዕድን ተቋም የጋራ ጥረት የተገኘው የዳይመንድ ማዕድን 73 ሚሊ ሜትር ርዝመት፣ 52 ሚሊ ሜትር ስፋትና 27 ሚሊ ሜትር ውፍረት እንዳለው ተገልጿል፡፡

በዓለም ትልቁ የዳይመንድ ማዕድን የተገኘው እኤአ በ1905 በደቡብ አፍሪካ ሲሆን፤ የጥራት ደረጃውም 3 ሺህ 1 መቶ 6 ካራት ሲሆን መጠሪያውም ኩሊናን ይባላል፡፡

በዓለም በመጠኑ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ የተቀመጠው እና በልዩ ስሙ ሌሴዲ ላ ሮና የተሰኘው የዳይመንድ ማዕድን የተገኘው እኤአ 2015 በሰሜናዊ ቦትስዋና ካሮዌ ግዛት መሆኑንና የጥራት ደራጃውም 1 ሺህ 1 መቶ 9 ካራት እንደነበር ተዘግቧል፡፡

ቦትስዋና የዓለም ሀገራት በኮሮና ምክንያት የጣሉትን የጉዞ ዕገዳ እያቀለሉ መሆኑንና የዓለም የጌጣ ጌጥ ገበያ ድጋሚ መከፈትን መነሻ በማድረግ እኤአ በ2021 ለዓለም ገበያ የምታቀርበውን የዳይመንድ ምርት በ38 በመቶ ለማሳደግ ማቀዷን አልጀዚራ ዘግቧል።