አመራሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመረዳት አገርን ለማሻገር መስራት ይጠበቅበታል ተባለ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) በየደረጃው የሚገኘው አመራር የአለምን፣ የሀገርን እና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት ሀገርን ለማሻገር መስራት እንደሚጠበቅበት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስገነዘቡ።

‘አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ – አዲስ አገራዊ እምርታ’ በሚል መሪ ሃሳብ ለድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በየደረጃው የሚገኘውን አመራር አቅም በየጊዜው በመገንባት የአገርን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚገባ በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ እና ብልፅግናዋን ዕውን ለማድረግ በየጊዜው የአመራሩን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ አመራሩ የዘመኑን ቴክኖሎጂና እና ዕውቀት መላበስ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ስልጠናው የሀገርንና የአስተዳደሩን ነዋሪዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ከንቲባ ከድር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሚቀጥሉት ቀናት በአገሪቱ የ10 አመታት መሪ ዕቅድ፣ በሚዲያና በኮሙዩኒኬሽን እንዲሁም በብልፅግና ፓርቲ ተቋማዊ ጥንካሬ ላይ ስልጠና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።