አርሶአደሮች በ3ኛው አረንጓዴ አሻራ መርኃግብር በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

ሰኔ 10/2013 (ዋልታ) – አርሶአደሮች በ3ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር በንቃት እንዲሳተፉ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡

በቢሮው ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት በክልል ደረጃ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር 1 ነጥብ 83 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸው፣ ሁሉም ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ መጠናቀቁን ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 184 ሺህ የችግኝ ተከላ ቦታ መዘጋጀቱንና ከ800 ሚሊየን በላይ የተከላ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ የተከላ ቦታ ካርታ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

ችግኞቹ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚተከሉ እና በደን፣ ጣምራ ደን እርሻና ስነ-ህይወታዊ ተከላ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡

ግራብሊያ፣ ዋንዛ፣ ባህርዛፍ፣ አመራላ፣ ወይራ፣ ዝግባ እና የሀበሻ ፅድ ለመትከል ከተዘጋጁ የችግኝ ዓይነቶች መካከል እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡

ችግኞችን የመትከል ሥራ በግለሰብ፣ በቡድን እንዲሁም በዘመቻ መልክ እንደሚካሄድም አቶ እስመለዓለም ተናግረዋል፡፡ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ሥራ ሁሉም በኃላፊነት እንዲሰራና የሚተከሉትንም እንዲያንከባክብ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የተከላ ተግባሩን ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የተቋቋመ ዐቢይ ኮሚቴ እና ቴክኒክ ኮሚቴ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡

በክልል ደረጃ “ኢትዮጵያን እናልብስ” በሚል መሪ ሃሳብ በአማራ ክልል 3ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ግንቦት 30/2013 ዓ.ም በደብረማርቆስ መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በዕለቱ ከ600 በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡

በባለፈው ዓመት 2ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውንና ከዛም ውስጥ 78 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን አስታውሰዋል፡፡

(በአድማሱ አራጋው)