አንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ሲታወሱ

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በ1942 ዓ.ም በሀድያ ዞን ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዛሬው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሾኔ እና ሆሳዕና፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዳማ አፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በ1965 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕይወት አግኝተዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ አቅንተው የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከቱሊን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

በደርግ ዘመነ መንግስት ማስተርሳቸውን ለመማር ወደ አሜሪካ ሲያቀኑ ወደ ሀገር ቤት ይመለሳሉ ብሎ የጠበቃቸው ሰው ባይኖርም እሳቸው ግን ሀገሬን ለማን ትቼ፤ እጣዬ በሀገሬ ነው በማለት ተመልሰዋል፡፡

ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በሀገረ አሜሪካ አጠናቀው ከመጡ በኋላም ኢንትሮዳክሽን ቱ ባዮሎጂ (Introduction to Biology) የሚል መጽሐፍ ጽፈው ለህትመት አብቅተዋል፡፡

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከቆዩ አንጋፋ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በተፎካካሪ ፓርቲ ፖለቲከኝነት ስማቸው በጉልህ ከሚነሳ ፖለቲከኞች መካከል ተጠቃሽ ሲሆኑ የደርግ መንግሥት ወድቆ በኢህአዴግ አስተባባሪነት በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ወቅት ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ለሁለት ዓመት አገልግለዋል፡፡

በሽግግሩ ወቅት የደቡብ ፓርቲዎችን አስተባብረው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲ ህብረት የተባለ የፖለቲካ ድርጅት በመመስረት 17 መቀመጫ ማግኘት ችለው እንደነበረ ይታወሳል።

አንጋፋው ፖለቲከኛ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር በመሆን እያገለገሉ ነበር፡፡

ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው ባሻገር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የድኅረ ምረቃ እና የዶክትሬት ተማሪዎችን አስተምረዋል። አማክረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር በመሆን የአካዳሚክ እና የምርምራ ሥራቸውን የጀመሩት በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የኢትዮጵያ ባዮሎጂካል ሶሳይቲ መሥራች እና ፕሬዝዳንት ነበሩ። የፓን አፍሪካ ባዮቲክስ ኢኒሼቲቭ ስራ አስፈጻሚ በመሆንም አገልግለዋል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ከ100 በላይ የምርምር ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ባለትዳር እና የልጆች አባት ነበሩ፡፡