ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና በመደጋገፍና በአንድነት ማለፍ ይገባል – ዶክተር ሊያ ታደሰ

ዶክተር ሊያ ታደሰ

ጥቅምት 11/2014 (ዋልታ) “በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና በመደጋገፍና በአንድነት ማለፍ ይገባናል” ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የጤና ሚኒስቴር በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ስራ ማስጀመሪያ የሚውል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የህክምና መርጃ መሳሪያ ዛሬ ድጋፍ ተደርጓል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ አፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተገኝተው ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የህክምና መርጃ መሳሪያዎቹን አስረክበዋል።

“በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና በመደጋገፍና በአንድነት ማለፍ ይገባል” ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለክልሉ የተሰጠው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።

ጤና ሚኒስቴር የህክምና መረጃ ቁሳቁስ ድጋፋ ያደረገው በክልሉ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው አምስት የጤና ተቋማት ስራ ለማስጀመር መሆኑ ነው የተገለጸው።

የሚኒስቴሩ ድጋፍ የህክምና ተቋማቱ ወደ ስራ እንዲገቡና ድንገተኛና መደበኛ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ እገዛ እንደሚያደርግ ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተደድር አወል አርባ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ንጹሐንን ገድሏል፤ የዜጎች ሀብት ላይ ዘረፋ ፈጽሟል።

ይህ አሸባሪ ቡድን ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እናቶችና ህጻናትን እየገደለ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም ከሰሞኑ በጭፍራ ወረዳ ላይ በከባድ መሳሪያ ድብደባ በመፈፀም እናቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ላይ ግድያ መፈጸሙን አስታውሰዋል።

የዚህ አሸባሪ ጨካኝና አረመኔ ቡድን ድርጊት ለታሪክ የሚቀመጥ መሆኑን ገልጸው፤ የጤና ሚኒስቴር በወሳኝ ወቅት ድጋፍ በማድረጉ ምስጋና ችረዋል። ይህ የአሸባሪ ቡድን ድርጊት “በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ይመከታል” ብለዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው አሸባሪው ህወሓት አፋርና አማራ ክልሎችን በመውረር ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸመ ሲሆን፣ ንጹሃን ሰዎችን ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፣ ሴቶችን ደፍሯል የንጹሐንን ህይወት ቀጥፏል።