ከተለያዩ ክልሎች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ምግብ እርዳታ እየቀረበ ነው-ኮሚሽኑ 

ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – በተለያዩ ክልሎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች የእለት ምግብ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌደራልና የክልል መንግስታት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም  ኮሚሽኑ ጠይቋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ ወገኖች ወደ ክልሉ በመምጣት ተጠልለው ይገኛሉ።

ሰሞኑን ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአጣየ፣ ሸዋሮቢትና አካባቢዎቻቸው በተፈፀመ ጥቃት ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

“በጥቃቱ የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፣ ከፍተኛ የሆነ ንብረት ወድሟል፣ በተፈናቀሉ ወገኖች ላይም ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ደርሷል” ብለዋል።

በአማራ ተወላጆች ላይ በየአካባቢው እየደረሰ ያለው ጥቃት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፣ ሁኔታው በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን አመልክተዋል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር ለተፈናቃዮች በየወሩ እስከ 60 ሺህ ኩንታል እህል ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡንና ባለሃብቶችን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብ እንዲያገኙ አቅም በፈቀደ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።