ከተማ አስተዳደሩ የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር ተወያየ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ እና ከተማዋን ለማልማት በዛሬው እለት ውይይት አካሂዷል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር በመተባበር፣ የሚችሉ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግና ሌሎችም በአቅማቸው ልክ ቤቶቹ ተገንብተው በተመጣጣኝ ዋጋ ተከራይተው የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው ጋር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ ባለሀብቶች የልማት አጋር እንደመሆናችሁ መጠን የተዘጋጁ ሞዳሊቲዎችን በዝርዝር በመመልከት ለተግባራዊነቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት ለመስራት እንቅስቃሴ ልታደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለመቅረፍ አምስት የቤት ግንባታ ሞዳሊቲዎችን በዝርዝር አዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ለማድረግ አጋርነታችሁን እየተጠባበቀ ይገኛል ሲሉም አክለዋል፡፡

ከንቲባዋ የቤት አልሚዎች በአጭር ጊዜ ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት የየድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የውጭ አገር አልሚዎችን የአዋጭነት ደረጃን በመፈተሽ እንዲሳተፉ ለማድረግ ይሰራልም ብለዋል፡፡

የቤት አቅርቦትን በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በዓመት ከ2 መቶ ሺሕ በላይ ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል ያሉት በምክትል ከንቲባ መዓረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ያስሚን ዉሀቢረቢ ናቸው፡፡

አሁን ያለው ወቅታዊ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ አልሚዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ የተዘረጉ ሞዳሊቲዎችን መሠረት በማድረግ ልትሰሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የግሉ ዘርፉ በተለይ በቤት ልማት የፌዴራል መንግሥትና ከተማ አስተዳደሩ የጀመሩትን በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ የለውጥ ሥራዎች መሠረት በማድረግ በሽርክና መስራት ከአልሚዎች ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት የሚሰራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጃቸውን አማራጭ የቤት ልማት ሞዳሊቲዎችን ለውይይቱ መነሻ በማድረግ ከሪል እስቴት አልሚ ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሂዶበታል፡፡