ክልሉ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ማድረጉ ተገለጸ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል በዘንድሮው አመት አረንጓዴ አሻራ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ ገለፁ፡፡
በክልሉ ባለፉት ሶስት አመታት 7 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውንና ከዚህ ውስጥ 72 በመቶው መፅደቁንም ገልጸዋል።
የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሚስራ አብደላ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን አስመልክተው እንደገለፁት በክልሉ ባለፈው አመት የተካሄደውን የአረንጎዴ አሻራ መርኃ ግብር በመገምገም በተለይም ከፅድቀት መጠን ጋር ተያይዞ የታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘንድሮው በሚከናወነው አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርም በክልሉ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ከሚተከሉ ችግኞች መካከልም 70 በመቶው የተለያዩ አይነት አትክልትና ፍራፍሬዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
አትክልትና ፍሬፍሬዎቹም በአርሶ አደሩ እርሻ ላይ ይተከላሉ ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ለዚህም በየቀበሌው ከሚገኝ አርሶ አደር ጋር ውይይት ተደርጎ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህም በዋናነት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የፅድቀት መጠንን ከማሳደግ አንፃር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
እየተደረጉ የሚገኙ ዝግጅቶች በሚመለከት ዋልታ ያነጋገራቸው የችግኝ ጣቢያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ መልኩ የተለያዩ ችግኞችን የማዳቀል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በክልሉ በአራተኛው ዙር መርኃ ግብር የተያዘው እቅድ እንዲሳካ በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር መሀመድ አባስ በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት
ሶስት አመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 7 ሚሊየን ችግኞች መተከሉን እና ከዚህ ውስጥም 72 መቶው የሚሆነው መፅደቁ ተናግረዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)