ዜጎች ከሳኡዲ አረቢያ በሚመለሱበት ሁኔታ ዙሪያ ምክክር ተደረገ

ሰኔ17/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከሳኡዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጋር ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር በሚመለሱበት ሁኔታ ዙሪያ ምክክር አደረገ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል በአቶ መስፍን ሻዎ የተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ጋር በመሆን ከሳኡዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ተሚሚ አል-ደውሰሪ እና ከሳኡዲ አረቢያ የአገር ግዛት ሚኒስቴር ልዩ የደህንነት አማካሪ ጄኔራል ጀምዓን አዛህራኒ ጋር በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብትና ደህንነት በሚከበርበት እና ወደ አገር በሚመለሱ ዜጎች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት አድርገዋል።

በዚህም መሰረት የሳኡዲ አረቢያን የድንበር ደህንነት ሥርዓት ጥሰው የገቡ፣ የአገሪቱን የመኖሪያ ፍቃድ እና የሥራ ፈቃድ ህግጋትን ተላለፈው የሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆና በገዛ ፍቃዳቸው በተፋጠነ ሁኔታ እና በሁለቱ አገራት መንግስታት የጋራ ትብብር ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት በቅርብ ቀን የሚጀመር ይሆናል።

የልዑካን ቡድኑ ከአምባሳደር ሌንጮ ባቲ እና በጄዳ የኢትዮጵያ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር አብዱ ያሲን ጋር በመሆን በጂዳ ሹመይሲ እስር ቤት ጉብኝት በማድረግ ታራሚዎች ያሉበትን ሁኔታ በመመልከት፣ በማነጋገር፣ በማበረታታት እና በቅርቡ ወደ አገር ቤት የሚመለሱ መሆናቸውን መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡