የመሬትን ጉዳይ በዘመናዊ መልኩ ለማቀናጀት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሐሰን ገለጹ

                                                                          ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሐሰን

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) የመሬትን ጉዳይ በዘመናዊ መልኩ ለማቀናጀት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሐሰን ገለጹ፡

4ኛው ክልል ዐቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ርዕሰ መስተዳድሩ እና የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አመንቴ ገሺ በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በፎረሙ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደ ሀገር ብሎም እንደክልል አያሌ ችግሮች እንዳጋጠሙ ጠቁመው ችግሮቹን ለመፍታት ከባለሃብቱ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በዘርፉ የታቀደውን ለማሳካት እንቅፋት እንደነበሩ ገልፀው ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመቅረፍ እና ሠላምን በማረጋገጥ ልማተን ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ባለሃብቱ በክልሉ መሬት ለማግኘት ለሚያቀርበው ጥያቄ በፍጥነት ምላሽ የሚያገኝ ቢሆንም መሬቱን ከተረከበ በኋላ ወደ ሥራ ያለመግባት ችግር የዘርፉ ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል።
ባለሃብቱ የክልሉን ጥሬ ሀብት ይዞ ስለመሄድ እንጂ ክልሉ ላይ የመገንባት እና የመስራት ፍላጎቱ ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ የክልሉ መንግሥት በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ማለታቸውን የቢሮው መረጃ ያመለክታል።
የቢሮው ኃላፊ በበኩላቸው ክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እምብርት ከመሆኑም ባሻገር የእምቅ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት በመሆኑ የሀገራችን የልማት ስበት ማዕከል እንደሚሆን ተስፋ እንደተጣለበት ገልጸዋል።