የመከላከያ ሠራዊት በሲቪሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ የወታደራዊ አቅሞችን ነጥሎ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተገለጸ

ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ

መስከረም 20/2015 (ዋልታ) የመከላከያ ሠራዊት በሲቪሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ በከፍተኛ ጥንቃቄና የዒላማ ጥራት የወታደራዊ አቅሞችን ነጥሎ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።

የህወሓት የሽብር ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጥቃት ለማስቆም መንግስት የመከላከል እርምጃዎችን ሲወሰድ መቆየቱን ገልጿል።

ይህንን ጥቃት ለመከላከል የሽብር ቡድኑን ወታደራዊ ዐቅሞች በተመረጠ ሁኔታ እና በከፍተኛ ጥንቃቄ ዒላማ በማድረግ የመከላከል ተልእኮውን እየፈጸመ ነው ብሏል።

የሽብር ቡድኑ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደቆየው ወታደራዊ አቅሙን እና አመራሮቹን በዕምነት ቦታዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ማኅበራዊ አግልግሎት መስጫ ቦታዎች እና ሲቪሎች በሚኖሩባቸው ቦታዎች እየደበቀ እንደሚገኝም ገልጿል።

በተጨማሪም የሽብር ቡድኑ የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች የሰብአዊ እርዳታ ተቋማትን ንብረቶች ለማጓጓዣነት እና ለመሳሪያ ማከማቻነት እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝም ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያው አመልክቷል።

የመከላከያ ሠራዊት በሲቪሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ በከፍተኛ ጥንቃቄና የዒላማ ጥራት የወታደራዊ አቅሞችን ነጥሎ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም አረጋግጧል።

አሁንም ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ዓዲ ዳዕሮ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በተመረጡ ዒላማዎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች እና ተተኳሾች ያሉበትን ቦታ ዒላማ አድርጎ እርምጃ መውሰዱን ጠቅሷል።

የሽብር ቡድኑ ህወሓትን ለማገዝ በታሪካዊ ጠላቶቻችን የተላከው አውሮፕላን ተመቶ ከወደቀበት ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ የአየር ክልል በኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥብቅ ቁጥጥር ሥር ይገኛል ሲልም ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።