የመገናኛ ብዙሃን በ6ኛው ምርጫ ዙሪያ በኃላፊነት መዘገብ ይገባቸዋል- የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች

 የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ንጉሴ መሸሻ

ኢትዮጵያ ቀጣይ የምታካሂደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ መገናኛ ብዙሃን ለመራጩ ማህበረሰብ ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያማከለ መረጃ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ፡፡

እንደ አራተኛ መንግስት የሚቆጠረው መገናኛ ብዙሃን ስልጣን በህዝብ ምርጫ የሚወሰንበት ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ንጉሴ መሸሻ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ንጉሴ አክለውም መገናኛ ብዙሃን ማህበረሰቡ ሃገሪቱን በብቃት እንዲሁም ዜጋውን በትጋት የሚያገለግለውን መንግስት ለመወከል ስለሚመርጠው የፖለቲካ ፓርቲ በቂ እውቀት እንዲኖረው ማድረግ ተቀዳሚ ስራው ሲሆን ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ባማከለ መልኩ የምርጫ ሂደቱን መዘገብ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የመራጩን ህዝብ ይሁንታ ለማግኘት የሚጓዙበት ጎዳና የግጥሚያ ዘይቤ፣ የፍልሚያ ትዕይንት የሚፈጥር እንዲሁም በማህበረሰቡ መካከል አለመግባባትን የሚያነግስ መሆን እንደሌለበት የተናገሩት ዶ/ር ንጉሴ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሃሳብና መልዕክት በሚገባ በመመልከት ለህብረተሰብ ጆሮ መጠንቀቅ ይገባል ብለዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የምርጫ መረጃዎችን ከማቅረብ በዘለለ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ ቁልፍ የሆነውን ፍትሃዊነት ተግባራዊ በማድረግ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ የውይይትና የክርክር መድረክ መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

                                                                      ሰጠኝ እንግዳው

ምርጫ ለአንድ ሃገር ዴሞክራሲያዊ ጎዳና ምሰሶ በመሆኑ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ፍትሃዊ እንዲሁም ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መረጃን የማድረስ የመገናኛ ብዙሃን ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምክትል ስራ አስፈፃሚ ሰጠኝ እንግዳው ገልጸዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ተቀዳሚ ትኩረት መሆን የሚገባው የቅድመ ምርጫ ተግባራት ላይ መሆኑን ገልፀው፣ ማህበረሰብ አሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሃሳብ የቃኘ ለሀገር እድገትና ብልፅግና የሚበጅ መሪ መምረጥ ያስችል ዘንድ በር ከፋች የሆነ መረጃን ማድረስ ይገባዋል ሲሉ ምክትል ስራ አስፈፃሚው ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን በሚፈጠርላቸው የውይይት መድረክ አንድነት አፍራሽ፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ሃሳቦችን ማንፀባረቅ እንደሌለባቸው እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን ይህን የሚያቃና ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

(በሄብሮን ዋልታው)