የብሄራዊ ቤተመጽሃፍት እና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ሰራተኞች በኮንታ ልዩ ወረዳ ችግኝ ተክሉ መጽሃፍት ለገሱ

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ)- የኤጀንሲው ሰራተኞች በደቡብ ክልል ኮንታ ልዩ ወረዳ በጨበራ ቀበሌ ተገኝተው ችግኝ የተከሉ ሲሆን በልዩ ወረዳዋ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶችም የመጽሃፍት እና የመማሪያ  ቁሳቁሶች ለግሰዋል።

የኮንታ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ  ፋንታሁን ብላቴ መጽሃፍት ለአእምሯችን ችግኝ ለምድራችን ይዘው ለመጡ የኤጀንሲው ሰራተኞች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በተያዘው የክረምት ወራት ችግኝ ተከላ መርሃግብር ወረዳው ከ8 ሚሊዬን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም አቶ ፋንታሁን ገልጸዋል።

የብሄራዊ ቤተመጽሃፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ  መዝገቡ የኤጀንሲው ሰራተኞች በኮንታ ልዩ ወረዳ ተገኝንተው 5 ሺ ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራቻቸውን እንዳሳረፉ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ከችግኝ በተጨማሪ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የሚጠቅሙ አጋዥ መጽሃፍትን እንዲሁም ጠረጴዛና ወንበር በስጦታ መልክ ይዘው ስለመምጣታቸው ገልጸዋል።

የተተከሉ ችግኞችን አመት ጠብቆ ከማየት ይልቅ በቅርበት መከታተል ይገባል ያሉት አቶ ይኩኖአምላክ ኤጀንሲያቸው የተተከሉ ችግኞችን የሚቆጣጠሩ አራት ባለሙያዎችን ከአካባቢ ማህበረሰብ ለመቅጠር ማቀዱንም አሳውቀዋል።

ክረምቱ ከገባ ጀምሮ እስካሁን በኮንታ ልዩ ወረዳ 3.6 ሚሊዬን ችግኞች መተከላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በልዩ ወረዳው ባሳለፍነው አመት ክረምትም ከተተከሉ ችግኞች 90 ከመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

(በእንየው ቢሆነኝ)