የተከፈተብንን ጥቃት ለመመከት መፍትሄው የተደራጀ ንቅናቄ -የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ጥቅምት 11/2014 (ዋልታ) የተከፈተብንን ጥቃት ለመመከት መፍትሄው የተደራጀ ንቅናቄ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን አለኝ የሚለውን ኃይል በማሰባሰብ በአፋርና በአማራ ክልሎች ባሉት ግንባሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል ብሏል።
በዚህ ጥቃትም በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል፤ ንብረት ዘርፏል፤ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጋዝ አርከፍክፎ አቃጥሏል፤ በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉም ማኅበራዊና ምጣኔሃብታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ አድርጓል ሲልም አክሏል።
ቡድኑ የተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ እንዳይደርሳቸው አድርጓል ያለም ሲሆን የሃሰት ፕሮፖጋንዳንም እንደ ዋነኛ መሳሪያው በመጠቀም ላይ ይገኛል ሲል አትቷል፡፡
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የአማራና አፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች በመንጋ የመጣውን ጠላት ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በመሆን በሚያኮራ መልኩ እየመከቱ ይገኛሉ ያለወ መግለጫው፤ በተለይም ዘራፊው ቡድን በውጫሌ፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦ ደላንታና ጭፍራ ግንባሮች ጦርነት የከፈተ ቢሆንም የጸጥታ ኃይሉና የሕብረተሰቡ የጋራ ጥምር ኃይል ይህንን ወራሪ ኃይልና ሰርጎ ገቦችን በጀግንነት እየመከተ ይገኛል ነው ያለው።
በሌሎች ግንባሮች ሽንፈትን እያስተናገደ የሚገኘው የሽብር ቡድን ያለውን ኃይል ሁሉ አሰባስቦ ወደ ወሎ አምጥቷል፤ ይህ ደግሞ የመጨረሻ ጥረቱ ነው ሲልም አክሏል፡፡
ዓላማውም ሕዝቡን ማስጨነቅና ማሸበር እንዲ ማሸነፍ አይደለም በማለትም ይህንን የሽብር ቡድኑን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመመከት የደቡብ ወሎና የአፋር ሕዝብ በተለይም ወጣቶች እያደረጉ ያሉት አኩሪ ተጋድሎ እጅግ የሚደነቅ ነው ብሏል።
ለፀጥታ ኃይሎች ደጀን ከመሆን ጀምሮ የሚሽሎኮሎኩ የጠላት ኃይሎችን በመመከት በየአካባቢው ለስለላ የተሰማሩ ፀጉረ ልውጦችንና ሰርጎ ገቦችን ተከታተሎ በመያዝ ታሪክ የማይዘነጋው ተጋድሎን እየፈጸሙ ይገኛሉም ብሏል የመንግሥት መግለጫ።
ጠላት ይህንን የሕዝብ አኩሪ ተጋድሎ ጥላሸት የሚቀቡ አፍራሽና ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳዎችን እየነዛ ነጻ አካባቢዎችን እንደተያዙ በማስመሰል ሕዝብን ለማሸበር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ያለው መግለጫው ሕብረተሰቡ በጠላት አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳይረበሽ የጀመረውን አገር የማስቀጠል ተጋድሎ በተደራጀ ንቅናቄ መመከት፣ አካባቢና ቀዬውንም ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ከጦርነት አካባቢ ውጪ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለዚህ ታሪካዊ ተጋድሎ አጋርነታቸውንና ደጀንነታቸውን እንደስከዛሬው ሁሉ እንዲያረጋግጡም መንግሥት ጥሪ አቅርቧል። ከመደበኛ የጦርነት አካሄድ በተቃራኒ የመጣን ኃይል ማንበርከክ የሚቻለው የተደራጀ ሕዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ነውም ሲል አፅንኦት ሰጥቷል።