የትምህርት ሥርዓትን የዲጂታል ኢኮኖሚው በሚፈልገው መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – የትምህርት ሥርዓትን የዲጂታል ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ማፍራት በሚያስችል መልኩ መከለስ እና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

“ወደ ዕውቀት-መር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ሀሳብ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ለትምህርት ዘርፉ በሚያደረገው አስተዋጽኦ ላይ በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ የትምህርት ሥርዓቱን የዲጂታል ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ማፍራት በሚያስችል መልኩ መከለስ እና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የዲጂታል ክህሎት የሌላቸው ዜጎች ከዲጂታል ኢኮኖሚው ለመጠቀም ያላቸው እድል የተገደበ እንደሚሆን ጠቅሰው፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂው የፈጠራቸውን መልካም እድሎች በመጠቀም የትምህርት አሰጣጡን እና አስተዳደሩን የተሳለጠ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል።

አክለውም የትምህርት ተቋማት ከመማር ማሰተማር እና ምርምር ባሻገር ለዲጂታል ኢኮኖሚው ስኬት ያላቸውን ጉልህ ሚና በመረዳት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

በፓናል ውይይቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለትምህርት ዘርፉ ያለው ሚና፣ የዲጂታል ክህሎት ፍኖተ ካርታ አተገባበር፣ መጻኢ ቴክኖሎጂዎች በትምህርት ስረዓቱ ላይ ያላቸው ፋይዳ እና በዲጂታል ትምህርት ሴክተሩ የሴቶች እና የግል ዘርፉ ሚና በሚል የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ውይይቱ የትምህርት፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን፤ ቴክኖሎጂን ለትምህርት ለምርምር እና ለአስተዳደር በዩኒቨርሲቲዎች፣ በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ለመጠቀም በሚያስፈልገው የዲጂታል ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።