የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ለኢትዮጵያ በሚያቀርበው የልማት ድጋፍ ዙርያ ሊወያይ ነው

ኢሞን ግሊሞር

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ለጊዜው ያዘገየውን ለኢትዮጵያ የሚያቀርበውን የልማት የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ በቀጣይ ወር ሊመክርበት ቀጠሮ መያዙን የኅብረቱ የሰብዓዊ መብት ተወካይ ኢሞን ግሊሞር ተናገሩ።

ተወካዩ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለመመልከት በኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝታቸውም ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ላይ ከሚሰሩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የረድኤት ድርጅቶች እንዲሁም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።
ከእነዚህ አካላት ጋርም በሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ተወካዩ የጠቆሙት።
በዚህም በተለይም ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል የተደረሰው የተኩስ ማቆም ውሳኔ ኅብረቱ በአዎንታ እንደሚቀበለው ገልጸው ሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመው የሰብዓዊ ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
ከዚህም አንጻር የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ቀውስ ለገጠማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው ለዚህም ሙሉ ፍቃደኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ለኢትዮጵያ የሚያቀርበውን የልማት ድጋፍ ገንዘብን ጨምሮ ለጊዜው ማዘግየቱን ገልጸው ጉዳዩ እየተጤነ መሆኑን መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በጉዳዩ ላይ የሚመክረው የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤትም እርሳቸው በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ተመርኩዞ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አጠቃላይ ግምግማ በማድረግ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ገልጸዋል።