የኢትዮጵያና ሩሲያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሏቸው ትብብሮች ማጠናከር

ጥቅምት 12/2014 (ዋልታ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን ከአምባሳደር ኢቪግኒ ተርኪንን ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም ሀገራቱ በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሏቸውን ትብብሮች ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መክረዋል፡፡
ነባር ትብብሮችን በማጠናከር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ሁለቱ ሀገራት ከቆየው ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባሻገር በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመሯቸውን ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡
አምባሳደር ኢቪግኒ ተርኪን በበኩላቸው፣ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በቴክኖሎጂው ዘርፍ በርካታ ፕሮጄክቶችን ነድፋ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ ባይሎጂካል ኤክስፒዲሽንና በምርምር መስክ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው አንስተዋል፡፡
በስነ-ህይወት ጥናት፣ በዓሳ እና እንስሳት እርባታ እንዲሁም በአፈር ለምነት ዙሪያም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በስፔስ ሳይንስ፣ በኒውክሌር ሳይንስ መስኮች እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
በቀጣይም የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድም በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለ የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የባይሎጂካል የጥናት ማዕከል መገንባት የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡