የኢንተርፕርነርሺፕ ባህል እየጎለበተ እንዲሄድ በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

ኅዳር 26/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነርሺፕ ባህል እየጎለበተ እንዲሄድ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት “ሚሊዮን ፈተናዎች፤ ሚልዮን እድሎች” በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፉ የስራ ፈጣሪዎች ሳምንት “የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት” ማጠናቀቂያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በዛሬው እለት ለስራ ፈጣሪዎች የሕግና ፓሊሲ ስነ-ምህዳር ምቹ ማድረግን በተመለከተ የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ጋራ እንቅስቃሴ መግባታቸው ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የመረጃ ተደራሽነትንና አገልግሎትን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ምርምር እና የፈጠራ ስራዎች በመከወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢንተርፕርነርሺፕ ባህል እንዲጎለብት ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የተቋማቱ የጋራ ስራዎች ለዚህ ስኬት በጥሩ ጅምር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው በሁነቱ በርካታ ልምድና ተሞክሮ መገኘቱን ገልጸዋል።
“በስራ ፈጠራ ዙሪያ ከተገኘው ልምድ አንፃር መልካም ልምዶችን በማስቀጠል ተግዳሮቶችን ደግሞ እየፈታን እንሄዳለን” ሲሉ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
አለም አቀፉ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ15ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ9ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።