የእስራኤል መንግስት ለተፈናቀሉ ዜጎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ   

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) የእስራኤል መንግስትና ሕዝብ በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች 14 ቶን የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

የእስራኤል መንግስት በአሸባሪውና ወራሪው ሕወሓት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎችና በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን ግምቱ 14 ቶን የሆነ የንጽህና መጠበቂያ፣ ክራንች፣ ዊልቼርና የተለያዩ የህክምና ቁሳቁስሶችን ለሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስርክቧል፡፡

በርክክብ ስነሥርአቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የእስራኤል መንግስትና ሕዝብ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፉ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪካዊ ወዳጅነት ከፍ ከማድረጉም በላይ በቀጣይ የሚኖረውን የላቀ ትብብርና ወንድማማችነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ከሕዝብ ለሕዝብ የተደረገ መሆኑንና የእስራኤል መንግስት በኢትዮጵያ በተለያዩ ችግር ውስጥ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማህበራዊና በጤና ዘርፎች እያደረገ የሚገኘውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡