የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16 (2) እንዲሰረዝ ተወሰነ

የካቲት 18፣ 2013 (ዋልታ) – የምርጫ እጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(2) ትርጉም ተዛብቶ በመወሰዱ መመሪያው እንዲሰረዝ መደረጉንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው የእጩዎች ምዝገባ በሚከናውንበት ወቅት በእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(2) ትርጉም ተዛብቶ በመወሰዱ የተለያዩ የምርጫ ክልሎች የመንግስት ሰራተኛ እጩዎችን ያለደምወዝ ፈቃድ የተወሰደበትን ሰነድ እንዲያቀርቡ ተጠይቋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተፈጠረውን መምታታት ለመፍታት እጩ የተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16 (2) እንዲሰረዝ መወሰኑን ገልጿል።

በዚህም ማንኛውም እጩ ለመመዝገብ ያለደምወዝ ፍቃድ የማያስፈልገው መሆኑን አጽንኦት በመስጠት የዚህን የአሰራር ክፍተት ለመድፈን ለምርጫ ክልል ጽ/ቤት አስፈጻሚዎች መልእክት እንዲተላለፍ የሚደረግ መሆኑንም አስታውቋል።

ቦርዱ ለ6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ እየተከናወነ ያለውን የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በማገናዘብ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትም እየሰራ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በመሆኑም በአዋጅ 1162/2011 እንዲሁም በእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(1) መሰረት የመንግስት ሰራተኛ እጩዎች ስራቸውን መልቀቅ ሳያስፈልጋቸው በእጩነት ለመወዳደር እንደሚችሉ ብሏል።

እጩ ከሆኑ በኃላም በምርጫ ወቅት ያለደምወዝ ፈቃድ የማግኘት መብታቸውም በህግ የተሰጠ እንደሆነም ተገልጿል።

ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባን በሚያከናውንበት ወቅት በእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(2) ትርጉም ተዛብቶ በመወሰዱ የተለያዩ የምርጫ ክልሎች የመንግስት ሰራተኛ እጩዎችን ያለደምወዝ ፈቃድ የተወሰደበትን ሰነድ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን በመረዳቱ አዋጁ እንዲሰረዝ መደረጉን ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።