የዓድዋ ድል ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለሚንቁ እንደሚዋረዱ ማሳያ ታሪክ ነው – ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

                         የ8ኛው ዙር የጉዞ አድዋ ተጓዦች ሽኝት

የዓድዋ ድል የአፍሪካዊያን ሁሉ ድል እንደሆነ እና ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለሚንቁ ሁሉ እንደሚዋረዱ ማሳያ የሆነ ታሪክ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በዛሬው ዕለት የ8ኛው ዙር የጉዞ አድዋ ተጓዦች ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡

በመርኃግብሩ ላይ የተገኙት ወ/ሮ አዳነች ለተጓዦቹ መልካም ጉዞ እንዲሆንላቸው ተመኝተው፣ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚሆኑ የተለያዩ ግብዓቶች፣ ለአባላት ለጉዞ ቆይታቸው የሚበቃ የምግብ ግብዓት እንዲሁም 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ ስም አበርክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፋይዛ መሀመድ በበኩላቸው፣ የዛሬ 125 ዓመት እንደዛሬ ትራንስፖት ባልነበረበት በአስቸጋሪ ዘመን አባቶችና እናቶች ከአራቱም አቅጣጫ ተሰብስበው ጣሊያንን ድል አድርገዋል፡፡

ይህን ለማስታወስ ደግሞ በየአመቱ የሚደረገው የዓድዋ መታሰቢያ ጉዞ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ተጓዦች በጉዟቸው ስለኢትዮጵያ አንድነትና ታሪክ ሰሪነት ለትውልድ መልዕክት እያስተላለፉ ጉዟቸውን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

(በስመኝ ፈለቀ)