ገበያ ተኮር የበግ ድለባ ሥራን በማከናወን የሴቶችና ወጣቶችን ኢኮኖሚ ማጎልበት ይገባል ተባለ

ኅዳር 27/2015 (ዋልታ) ገበያ ተኮር የበግ ድለባ ሥራን በማከናወን የሴቶችና ወጣቶችን ኢኮኖሚ ማጎልበት እንደሚገባ በዓለም አቀፍ ቆላማ አካባቢዎች የግብርና ምርምር የሚያደርገው ኢካርዳ (ICARDA) ገለጸ፡፡

ለዝርያ የማያስፈልጉ በጎችን በማድለብ ገቢ መፍጠር እንዲቻል የአርሶ አርብቶ አደሩንና ወጣቶችን ግንዛቤ ሚዲያን በመጠቀም ማሳደግ የሚያስችል ስልጠና በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ ለሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሰጠ ነው፡፡

በኢካርዳ የምርምር ባለሙያው ሙሉቀን ዘለቀ በመድረኩ እንደገለጹት ባለፉት ጊዜያት 1 ሺሕ 80 ሴቶችና ወጣቶች የድለባ ሥራን በመስራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሣደግ እንዲችሉ አድርጓል ፡፡

የእነዚህ ወጣቶችን ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋት እንዲቻል ሚዲያዎች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በስልጠናው ለ2 ቀናት የሚቆይ ሲሆን የሚዲያ ባለሙያዎችን የአረካና ቦንጋ ግብርና ምርምር የእንስሳት ተመራማሪዎች እየተሳተፉ የደሬቴድ ዘገባ አመላክቷል፡፡