ጠ/ሚ ዐቢይ መንግስት ከሸኔ ጋር ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት እንዳለው ገለጹ

ጠ/ሚ ዐቢይ

መጋቢት 19/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግስት ከሸኔ ጋር ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት እንዳለው ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሸኔ ጋር የተጀመረው የሰላም ሂደት ምን ደረጃ ላይ ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡

ከሸኔ ባለፈ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ እና ቅማንት አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩ እንደሆነም አንስተዋል።

ባለፉት ጊዜያት ከሸኔ ጋር ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከ10 ጊዜ በላይ ሙከራዎች ቢደረጉም ኃይሉ በአንድ ተደራጅቶ የሚገኝ ባለመሆኑ የሰላም ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።

ሰላምን የሚጠላ የለምና የሰላም ሂደቱ እንዲሰምር አስፈላጊው ሁሉ ጥረት ይደረጋል እየተደረገም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላም እንዲመጣ አበክረን እየሰራን በመሀል ደግሞ የዜጎች ህይወት ህልፈት እና መፈናቅል እንዳይቀጥል በአካባቢው የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎቻችን አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እየወሰዱ ነው ብለዋል።

በትዕግስት ዘላለም