ጠ/ሚ ዐቢይ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ በዘላቂነት የሚፈታው በመሬት ላይ ድንበር የማካለል ስራ ሲሰራ ነው አሉ

መጋቢት 19/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ግጭት በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው የሁለቱ አገራትን ድንበር መሬት ላይ የማካለል ስራ ሲሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት በጉዳዩ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ከሱዳን መንግስት ጋር በመተባበር በሰላማዊ መንገድ ጉዳዩን ለመፍታት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ተቋቁሞ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱም አገራት በኩል ግለሰቦች እና አርሶ አደሮች መጉላላት እንዳይገጥማቸው በሚል በጋራ ስምምነት ያለ ቢሆንም በአፈጻጸም ደረጃ የታዩ ስህተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ግን በንግግር እና በውይይት ብቻ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከምክር ቤቱ አባላት ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ስለመፈፀሟ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ”ደቡብ ሱዳን የሰው አገር ለመውረር የሚያስችል ፍላጎት የላትም፤ በወረራ መንገድ ባይቆጠር ጥሩ ነው” ብለዋል፡፡

ነገር ግን በደቡብ ሱዳን ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን እና መንግስትም ጉዳዩን እንደሚያውቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ