ጠ/ሚ ዐቢይ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የተጀመሩ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገለጹ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

መጋቢት 19/2015 (ዋልታ) የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የተጀመሩና እየተተገበሩ የሚገኙ መፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ማተኮርና የምርት አቅርቦት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው ንረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እየጎዳ መሆኑን በጽኑ እንገነዘባለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩ ላለፉት 20 ዓመታት የማያቋርጥ የዋጋ ንረት በመፈጠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ሸማች እና አምራች መካከል ያለውን ክፍተት ማስተካከል አልተቻለም፤ ጦርነት፣ ድርቅ፣ የአጋር አካላት እርዳታ መቀነስ እና ወደ ከተማ ፍልሰት መጨመር ዋና ዋና የዋጋ ንረት ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ማጋጠሙን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ለመፍታት በርካታ የግብርና ምርቶች እንዲገቡ እየተደረገ እንደሆነና የዋጋ ንረት የተፈጠረውም የምርት እጥረት ኖሮ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዘህም በምርት ዙሪያ ባስጠናነው ጥናት ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት እስከ 1 ሺሕ ኩንታል ምርት ቤታቸው ያስቀመጡ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

ስንዴ ከታሰበው በላይ መመረቱንና በቂ ምርት መኖሩን ገልጸው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ሚዛናዊ የግብይት ስርዓት መከተል ይገባል፤ ምርት በማከማቸት የከተማው ነዋሪ እንዲቸገር ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡