ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ብሔራዊ ውይይቱ የሕዝብን ድምፅ በማዳመጥ ጫፍ የረገጡ ሐሳቦችን ለማቀራረብ እንደሚጠቅም ገለፁ

ጥር 6/2014 (ዋልታ) በአገር ዐቀፍ ደረጃ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የብሔራዊ መግባባት ውይይት ጫፍ እና ጫፍ የረገጡ ሐሳቦችን ለማቀራረብ ያስችላል ሲሉ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ገለፁ።
“በተለያዩ ምክንያቶች በሕዝቡ መካከል የተፈጠሩ ፅንፎች በመኖራቸው በአገራችን ትናንሽ ጉዳዮችም ጭምር እየገዘፉ የጭቅጭቅ ምንጭ ሲሆኑ ይታያሉ” ያሉት ፖለቲከኛው “አንዳንዶቹም ሐሳቦች የማይቀራረቡ የሚመስሉ ናቸው” ብለዋል።
ስለሆነም የሚደረገው ውይይት ጫፍ እና ጫፍ የረገጡ ሐሳቦችን በማቀራረብ ወደ መሃል እንዲመጡ የማድረግ አቅም አለው የሚል እምነት ነው ያላቸው።
በሚደረገው ምክክር እና ውይይት በተቻለ መጠን የሐሳብ መቀራረብ መፍጠር እንዲቻል በታላላቅ ከተሞች ከሚደረግ የታዋቂ ሰዎች እና ልሂቃን ውይይት ባለፈ እስከ ወረዳ ብሎም ቀበሌ ድረስ ወርዶ ሕዝቡን ተደራሽ ያደረገ ውይይት መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ብሔራዊ መግባባት ሰፊ እንድምታ ያለው ጉዳይ በመሆኑ ረዘም ያለ ውይይት እና ምክክር የሚፈልግ እንጂ በጥቂት ጉባኤዎች የሚቋጭ ጉዳይ አይደለም በማለትም በየደረጃው የሚገኘው ሕዝብ ድምፅ በአግባቡ እንዲደመጥ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያለው።
ከኢፕድ ጋር ቆይታ ያደረጉት አንጋፋው ፖለቲከኛ ምክክሩ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝ ውይይቱን የሚመሩ አካላት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ እና በሂደቱ የሕዝብን ሐሳብ ማካተት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አጀንዳዎች ምን ምን ናቸው የሚለውን መለየት እና በሂደቱ ላይ ማን ከማን ጋር በምን ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ መድረስ አለበት የሚለውም በዝርዝር መታየት አለበት ብለዋል።