በመዲናዋ የሚገኙ ሰማያዊ በነጭ ላዳ ታክሲዎችን ለመቀየር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ከአዲስ አበባ ታክሲ ላዳዎች ማህበር ጋር  በከተማዋ የሚገኙ ሰማያዊ በነጭ ላዳ ታክሲዎች ለመቀየር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

አዳዲሶቹ የትራንስፓርት አማራጭ መኪኖች ነዳጅ ቆጣቢ ከመሆናቸው ባሻገር ለአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው ተብሏል።

የትራንስፓርት ዘርፋን ለማሳደግም አዳዲሶቹ መኪኖች ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ትራንስፓርት ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር ስጦታው አካለ በከተማዋ የሚገኙ የላዳ ታክሲ ማህበራት ላለፋት አራትና አምስት አስርት አመታት በከተማዋ ሲሰጡ የቆዩት አገልግሎት የጎላ ነው ነበር ያሉ ሲሆን አሁን ላይ ግን ከእድሜም ከቴክኖሎጂም አኳያ የቆዩ በመሆናቸው መቀየራቸው ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ዘርፋን ለማሳደግና ለደንበኛው ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትም አዳዲሶቹ መኪኖች ሚናቸው የጎላ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ አበበ መኪናዎችን ከአጋሮቻችን ጋር በመተባበር በፍጥነት ለማቅረብ እንሰራለን ብለዋል።

የላዳ ታክሲዎች ማህበር ሰብሳቢ ቢኒያም መለሰ የላዳ ታክሲዎቹ በዘመናዊ መልኩ ተቀይረው መስራታቸው ለአሽከርካሪውም ሆነ ለከተማዋ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታክሲዎቹን ለመቀየር ከ6 በሊየን ብር በላይ የማመቻቸት ስራ መስራቱ ተጠቁሟል።

(በሱራፌል መንግስቴ)