ባንኩ ከየትኛውም ወገን ለሚሰነዘሩበት የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ የመከላከል በቂ አቅም እንዳለው ተገለጸ

 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ

መጋቢት 13/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውንም የሳይበር ጥቃት የመቋቋም በቂ አቅም እንዳለው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ በባንኩ ላይ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም የደረሰው ክስተት ከሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ እንጂ የሳይበር ጥቃት መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አለመኖሩን አስታውቀዋል።

በቅርቡ በባንኩ ላይ የተከሰቱ ችግሮችም በምርመራው ወቅት የተለዩ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ ይህም ባንኩ በሞባይል ሲስተሙ ላይ ማሻሻያ በሚያደርግበት ወቅት በተፈጠረ ስህተት የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

ምንም ዓይነት ከውጭ ወደ ባንኩ ሰርጎ በመግባት ጉዳት ያደረሰ ጥቃት አለመኖሩን ገልጸው አስተዳደሩ ተጨማሪ ምርመራዎችና የፎረንሲክ ስራዎችን በማከናወን ውጤቱን ለህብረተሰቡ በቀጣይነት እንደሚያሳውቅም አንስተዋል።

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ባንኩ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ተጨባጭነት የሌለው በመሆኑ ህበረተሰቡ መደናገጥ እንደሌለበት አሳስበዋል።

አስተዳደሩ በሀገሪቱ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃቶች እንዳይከሰቱ እየሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

በታምራት ደለሊ