በህዳሴ ግድብ ሙሌት ምክንያት በሱዳንና በግብጽ ህዝቦች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አይደርስም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ሐምሌ 2፣ 2013 (ዋልታ) – በታላቁ የህዳሴ ግድብ ሙሌት ምክንያት በሱዳንና በግብጽ ህዝቦች ላይ የሚደርስ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡

ግድቡ ለሶስቱ አገራት የትብብር እንጂ የጠብ መንስዔ ሊሆን አይገባም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ላይ በአረብኛ ቋንቋ ባሰፈሩት መልዕክት፡፡

የግድቡ ሙሌት በሚካሄድበት ወቅት ከውሃው ፍሰት ወደ ግድቡ የሚቀር ውሃ ካለም ጥቂት በመሆኑ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚደርሰ ጉዳት አይኖርም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የግድቡ መገንባት በተለይ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በክረምት ወቅት የሚከሰትን የጎርፍ አደጋ በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም የህዳሴ ግድብ መገንባት የተረጋጋ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ በሱዳን ሮዘሪስ ግድብ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን የጎርፍ አደጋ ስጋት ይቀንሳል ብለዋል፡፡

የትብብር ምንጭ ተደርጎ ከተወሰደ ግድቡ በቀጠናው የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት እንደሚያግዝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡