በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መቋረጥ ብዙ ጎብኚ ያላቸው ድረ-ገጾች እክል ገጠማቸው

ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መቋረጥ

ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ብዙ ጎብኚ ያላቸው ድረ-ገጾች ሐሙስ ዕለት ከሥራ ውጭ ሆነው እንደነበር ተገለጸ።

አንዳንድ ድረ-ገጾች ለመጎብኘት የሞከሩ ጎብኚዎች የዲ ኤን ኤስ ችግር መኖሩን መልዕክት ደርሷቸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ድረ-ገጾች መካከል ኤርቢኤንቢ፣ ዩፒኤስ፣ ኤችኤስቢሲ ባንክ፣ ብሪቲሽ ኤርዌይስ እና የፕሌይስቴሽን ድረ-ገጾች ይገኙባቸዋል ተብሏል፡፡

ከታዋቂዎቹ የዲ ኤን ኤስ አቅራቢዎች አንዱ የሆነው አካማይ ቴክኖሎጂስ በዲ ኤን ኤስ አገልግሎቱ ላይ “አንድ ችግር ተከስቷል” ካለ በኋላ ችግሩ መቀረፉን አስታውቋል።

የበይነመረብ መቋረጥን የሚቆጣጠረው ዳውንዴክተር በሺህዎች የሚቆጠሩ ችግሮችን በተመለከተ ከተጠቃሚዎቹ ሪፖርት እንደደረሰው ገልጿል።

በአውሮፓ እና በአሜሪካ አንዳንድ ድረ-ገጾች እንደገና መሥራት ጀምረዋል። በእስያ ሃገራት ያሉት ግን ችግሮች መኖራቸውን ሪፖርት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

ዲ ኤን ኤስ የምንጠቀምባቸውን በሰው-ተነባቢ የሆኑ እንደ bbc.com ያሉ የድረ-ገጽ አድራሻዎችን ወደ ኮምፒውተር ሰርቨር አመላካች አድራሻዎች ይለውጣል። በሂደቱ ላይ ችግር ሲገጥም አንድ ሰው የሚፈልገውን ይዘት ማግኘት አይችልም ማለት ነው።

ዳውንዲቴክተር ችግር እንደገጠማቸው ሪፖርት ካደረጋቸው አገልግሎቶች መካከል ባንኮች ፡- ባርክሌይስ፣ ሎይድስ፣ ቲ ኤስ ቢ እና ሃሊፋክስ፤ የጌም አገልግሎት ሰጪዎች ፡- ስቲም፣ ኮል ኦፍ ዲዩቲ እና ኢኤ፤ መገናኛ ብዙሃን ፡- ቻናል 4 እና አይቲቪ ይገኙባቸዋል ብሏል፡፡

እንደዚህ ያለ ሰፊ የአገልግሎት መቋረጥ ሲያጋጥም በሁለት ወራቶች ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

በሰኔ ወር የክላውድ ኮምፒውቲንግ አገልግሎት አቅራቢው ፋስትሊ የአገልግሎት መቆራረጥ ገጥሞት የነበር ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን እና የመንግሥት ጨምሮ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ድረ-ገጾች ሥራ እንዲያቋርጡ አስገድዶ ነበር ተብሏል።