ለ2013 ዓ.ም ተመራቂዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት

ለ2013 ዓ.ም ተመራቂዎችከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት፦

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሩቃንና ሥልጠና አጠናቃቂዎች፤

ወቅቱ በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር መሰረት የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሩቃንንና ሰልጣኝ አጠናቃቂዎችን መርቀዉ ወደ ቀጣይ የሕይወት ምዕራፍ ሽግግር መልካም ምኞታቸዉን የሚገልጹበት ነዉ።

ከተለያዩ የሀገራችን ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የዘመኑ ተመራቂዎችና የስልጠና አጠናቃቂዎች እንዲሁም ወላጆችና ቤተ-ዘመዶች፤ ደማቅ በሆነዉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ላይ ያላችሁ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ።

በተለይም፤ የመጀመሪያ ዙር ለሆነላችሁ ምሩቃንና ሰልጣኞች፤ ይህ ወቅት የድካማችሁን ፍሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ያያችሁበት ወቅትና የላቀ ደስታ የሚሰማችሁ በመሆኑ፤ በድጋሚ ለዚህ ታላቅ ደስታና የሕይወት ምዕራፍ እንኳን አደረሳችሁ።

በ2013 የትምህርትና ሥልጠና ዘመን በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችን በመቋቋም ምሩቃንንና ሥልጠና አጠናቃቂዎችን ለወቅቱ ደማቅ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት እያበቃችሁ ያላችሁ፤ የሀገራችን የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት መምህራንና አሰልጣኞች፤ የትምህርትና ሥልጠና የሥራ መሪዎችና ባለሙያዎች፤ የተማሪዎች የምግብ ቤት፤ የክሊኒክና የጊቢ ደህንነት ጥበቃ ሰራተኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት አካባቢ ማህበረሰብ የሰላምና የልማት አማካሪ ምክር ቤት አባላት በሙሉ፤ እናንተ በትብብር፤ በትስስርና በቅንጅት በመሥራት በኢትየዮጵያ ሰብዓዊ ካፒታል ዕድገትና ልማት ጉዞ የምታበረክቱት አስተዋጽኦ ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ፤ ምሥጋናችን እጅግ የላቀ መሆኑን ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

የሰዉን ልጅ በተለይም ወጣቱን በዕዉቀት፤ በክህሎትና በስብዕና በመቅረጽ ሂደት የምታኖሩት አሻራ የነገዋን ዕዉቀት-መር የኢትዮጵያን ማህበረሰብ የመገንባት ጉዳይ ነዉ፡፡

ወድ ምሩቃንና ሰልጣኝ አጠናቃቂዎች፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በርካታ ፈተናዎችን እየተሻገረች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያን ከጀግኖች አባቶቻችን እንዴት እንደተረከብን የታሪክ ምሁራንና አባቶቻችን አስተምረዉናል፡፡

በእዉነቱ፤ ለማንም ያልተንበረከከች ሉዓላዊት ሀገር ነበረች፤ አሁንም ነች፤ እንደዚሁም ስለመቀጠሏ የምንወስነዉ እኛዉ የዘመኑ ባለቤቶችና ባለአደራዎች ነን፡፡

ዛሬ ላይ፤ ሉዓላዊነቷን ለመንጠቅ ከዉስጥና ከዉጭ በርካታ ኃይሎች እየተፈታተኗት ይገኛሉ፤ ድንበራችንን ከማለፍ ባሻገር፤ እስከ ደጃፋችን ደርሰዉ ሊያጠቁን ይፈልጋሉ፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ተደጋጋሚ ፈተናዎችን የመሻገር ልምድ ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን፤ ፈተናዎቹ በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ሲደጋገም ተገቢነት የለዉም፤ ምክንያቱም የሁሉም ዜጋ የህልዉና ጉዳይ አደጋ ላይ በመሆኑና አባቶቻችን ያስረከቡንን ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችና በጽኑ መሰረት ላይ ያደረገች ሀገር ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የማሻሻገር ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት ጉዳይ በመሆኑ ነዉ፡፡

ጀግናዉ መከላከያ ሰራዊታችንና አጠቃላይ  መዋቅር ደጀን ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ሉዓላዊነቷን የሚፈታተነዉን ኃይል አደብ እንዲገዛ ማድረጉ ሩቅ አይሆንም፡፡

ሆኖም ግን፤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሉዓላዊነት መገንባት ቀጣይ የቤት ሥራችን በመሆኑ፤ እናንተ ምሩቃንና ስለጠና አጠናቃቂዎች ሚናችሁን ልትወጡ ይገባል፡፡

ምሁራን፤ ምሩቃንና ሰልጣኞች፡-

ዕዉቀት-መር ማህበረሰብና ፖሊቲካል-ኢኮኖሚ መገንባት ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ግንባታና ዘላቂነት ቀዳሚ መሳሪያ ነዉ ብለን እናምናለን፡፡

በዕዉቀት፤ በክህሎትና በጥበብ የበቃ ማህበረሰብና የበለጸገ ኢኮኖሚ መገንባት ተነጣጥሎ ሊታዩ አይገባም እንላለን፡፡

ይህ እዉነት ሊሆን የሚችለዉ ደግሞ ከመማርና ከመሰልጠን ባሻገር፤ ዕዉቀታችንን፤ ክህሎታችንና ጥበባችንን በተገቢዉ ለሀገራችን ዕድገትና ልማት ግብዓት አድርገን በመጠቀም ምጣኔ ይወሰናል፡፡

ጀግናዉ ሰራዊታችን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተለያዩ ግንባሮች እየተዋደቀ ይገኛል፡፡

እናንተ የዕዉቀት መሳሪያ የያዛችሁ ደግሞ በሰለጠናችሁበት ሙያ በቅንነትና በታታሪነት ሀገራችንና ሕዝባችንን ያለቅድመ-ሁኔታ በታማኝነት ካገለገላችሁ፤ በኢኮኖሚዉ ግንባር  ድጋፋችሁ የጎላ ይሆናል፡፡

ምሩቃንና ሰልጣኞች፡-

በሀገራችን አዲስ ምሩቅና ሰልጣኝ የመንግሥት ሥራ መያዝ ወይም የመንግሥት ሰራተኛ መባልን ከስምና ዝና ጋር ያዛመደ ይመስላል፡፡

ሆኖም ግን፤ እዉነቱ ከትምህርትና  ሥልጠና በኋላ የተፈጠረዉን አቅም፤ ብቃትና ስብዕና እንደአንድ ካፒታል አካል በመቁጠር፤ ከሌሎች ተጓዳኝ የሀብት ምንጮች ጋር በማዳመር የተሻለ ሥራና ገቢ በሚያስገኙ መስኮች ያለብክነት መሰማራትን የሚያካትት መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡

አዳዲስ ምሩቃንና ሰልጣኞች፤  እስካሁን ያገኛችሁትን የዕዉቀትና የክህሎት አቅምና ብቃት በመጠቀም፤ ሥራ ዕድል ለመፍጠር፤ ሀብት ለማመንጨትና ባለጸጋ ለመሆን በርካታ አማራጮችን ኢትዮጵያ እየዘረጋች ነዉ፡፡

ይህን ለማየትና ለመገንዘብ የሚቻለዉ፤ ከዚህ በኋላ የሚኖራችሁን የሕይወት ምዕራፍና አማራጭ መንገዶችን የመምረጥና የመወሰን አቅምና ብቃት፤ ጊዜን ያማከለ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጊዜ እጅግ በጣም ዉድ ሀብት ነዉ፤ ከጊዜ ጋር አብሮ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡

የተለመደዉን፤ “በሥራ አላገኘሁም እና በሥራ አልፈጠርኩም”  አባባሎች መካከል ያለዉን ሰፊ ልዩነት የሚሞላዉ ያካበታችሁት ዕዉቀትና ክህሎት ሊሆን ይገባል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ዕዉቀት-መር ኢኮኖሚ እየገሰገሰች ትገኛለች፡፡

ይህ ደግሞ የዕዉቀትና የክህሎት ባለቤት የሆኑትን እንደእናንተ ዓይነት ዜጎችን በጽኑ ትፈልጋለች፡፡

ኢትዮጵያ መንገዷንም መዳረሻዋንም ለይታለች፤ ጉዞዋንም ጀምራለች፡፡

ዕዉቀት-መር ማህበረሰብ ግንባታ ለፖሊቲካል ኢኮኖሚ ልህቀትና ዘላቂ የአገር ሉዓላዊነት  ወሳኝነቱ ሊረጋገጥ የሚችለዉ፤ ዕዉቀታቸሁና ክህሎታችሁ በተግባር ሲታይ ብቻ ነዉ፡፡

ዕዉቀት-መር ማህበረሰብ መገንባት፤ ለዕዉቀት-መር ፖሊቲካል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚኖረዉን ፋይዳ በአግባቡ ያለመገንዘብ የዋህነት ነዉ፡፡

የብዙ ታዳጊ ሀገሮች፤ ዕድገታቸዉና ልማታቸዉ ዘገምተኛ ሆኖ ባለበት የሚሄደዉ፤ ምንም እንኳን ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ቢኖሩም፤ በዋናነት ግን፤ ማህበረሰባቸዉን የማንቃት ኃላፊነትን በአግባቡ ሳይወጡ፤ ለረዥም ዘመናት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም የረዥምና አጭር ዘመን ዕቅድ ያለበቂና ብቁ ፈጻሚ ዝግጅትና ስምሪት ለማከናወን የሚታትሩ በመሆኑ ነዉ፡፡

ሀገራችንም፤ ይህን ዓይነት አዙሪት ባለፉት በርካታ ዓመታት አስተናግዳለች፡፡

ስለሆነም፤ ዕዉቀት-መር ማህበረሰብና ፖሊቲካል ኢኮኖሚን ነጣጥሎ ማየት፤ የአገሮችን ዕድገትና ልማት እንዲሁም ብልጽግና በእጅጉ እንደጎዳ፤ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ማስታወሱ በቂ ይመስለኛል፡፡

ሰፊ መሬት፤ የወሃ ሀብት፤ የተመቻቸ የአየር ንብረት ያላት ኢትዮጵያ የዕፅዋትና የእንስሳት ልማት በዕዉቀት፤ በክህሎትና በጥበብ ያልመራች በመሆኗ፤ ፈጠራና ቴክኖሎጂ የመጠቀም ደረጃዋ ዝቅተኛ በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን ከተጨባጭ አቅም አንጻር በበቂ መጠን የማሳደግ ዕድል እስካሁን አጋጥሟት አያዉቅም፡፡

ለራሷ ዜጎች እንኳን በበቂ መጠን ምርት ማቅረብ አልቻለችም፡፡ እንደእኛ ደሃ የነበሩ አገሮች፤ ዛሬ ላይ የበለጸጉት እርሻቸዉንና ግብርናቸዉን በዕዉቀት፤ በፈጠራና በቴክኖሎጂ በማዘመን ዜጎቻቸዉን ከመመገብ አልፎ ለአለም ገበያ በአቅራቢነት እስከመምራት ደርሰዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ከተመለከትን፤ በደከመና የሰዉን ጉልበት በሚፈጅ ያረጀ ተክኖሎጂ በመጠቀም ወደምርት እንቀይራለን፡፡

ለምሳሌ ያህል፤ ደኖቻችንን ተጠቅመን የቤትና የቢሮ ቁሳቁስ እንኳን በጥራት ለማቅረብ ባለመቻል፤ በገቢ ገበያ አቅርቦት ተወስነናል፡፡

ጥጥና ቆዳ አምራች ሀገር ሆነን ሳለ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን አብዛኛዉን ግብዓት ከዉጭ የሚያስገቡ በመሆኑ በኋልዮሽ ትስስርና በእሴት ሰንሰለት የሀገራችን ተጠቃሚነት ምጣኔ በሚፈለገዉ ደረጃ ላይ አይደለም፡፡

የማዕድናት ሀብት ልማታችን ከፍተኛ ካፒታልና ዕዉቀት የሚፈለገዉን ለጊዜዉ በሌሎች አማራጮች ማየቱ አግባብ ቢሆንም፤ በአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ በበርካታ ወጣት ምሩቃንና ሰልጣኞች ሊለሙ የሚችሉ  ማዕድናትን እሴት ከመጨመር ይልቅ በጥሬዉ በማቅረብና መጠነኛ ገቢ በማግኘት ላይ የተወሰነ ሆኖ ዘልቋል፡፡

ለዚህም፤ ዋናዉ የመፍትሄ  አካል መሆን የሚችለዉ በተለዩ አዋጭ አማራጮች ተግባር-ተኮር የክህሎት ሥልጠና ማበራከትና መጠነኛ መነሻ ካፒታል ማቅረብ ነዉ፡፡

እንደእኛ ባሉ በአብዛኛዉ የሕዝብ ድርሻ በወጣቱ በሚወከልበት ኢኮኖሚ፤  በአይሲቲ መስክ ለዜጎች የሚፈጠረዉ የሥራ ዕድል በየዓመቱ በርካታ ቢሆንም፤ የክህሎት ልማታችን በሚፈለገዉ የተግባር ሥልጠና ሳይሆን በንድፈ-ሐሳብ የታጨቀ በመሆኑ፤ በአገርዉስጥና ከአገር ዉጭ ባሉ የሥራ ዕድሎች ያለንን ተሳትፎ ዝቅተኛ አድርጓል፡፡

የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ የዘለቀዉና በርካታ መልካም ዕድሎች ያሉት፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የዉጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የሀገር ዉስጥ ተዋናዮች እየተበራከቱ ቢመጡም፤ በተሻለ ዋጋ የሠራተኛ ዕዉቀትና ክህሎት ለመጠቀም ባቀዱት ልክ ምርታማ ሆኖ ያለማግኘት ኢንዱስትሪዎችም በተቻለ  ፍጥነት እንዳያድጉ እንቅፋት ሆኖ እንደቆየ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ምርታማና ትርፋማ የሆነ ኢንዱስትሪ እስካልተፈጠረ ድረስ ዕዉቀትና ክህሎት አቅራቢዉ ሰራተኛና ባለሙያ በበቂ መጠን ሊከፈለዉ አይችልም፡፡

በኢንዱስትሪዎቹ መቋቋም ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ያሉ ቢሆንም፤ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ከግብዓት እስከ ምርት ድረስ ባለዉ የእሴት ሰንሰለት፤ ሀገራዊ ተሳትፏችን እጅግ አናሳ በመሆኑ፤ ሥራና ሀብት የመፍጠር ዉጤታማነታችን ደካማ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ለዚህም፤ በእያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ የእሴት ሰንሰለት በሀገር ዉስጥ አቅም ሊቀርብ የሚገባ ግብዓት፤ ሊፈጠር የሚገባ የሥራ ዕድልና ካፒታል እንዲሁም ሊተካ የሚገባ የገቢ ገበያ አቅርቦት ዕዉቀት-መር ነዉ ማለት አይቻለም፡፡

ይህን ጉድለት ማረም፤ እንደእናንተ ላሉ የዕዉቀት፤ የክሎትና የጥበብ ባለጸጋዎች ሌላ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራልና፤ ጥረታችሁንና ትጋታችሁን ልታክሉበት ይገባል እላለሁ፡፡

የሀገራችን የቱሪዝም ልማት ዘርፈ-ብዙ አማራጮች ያሉት በመሆኑ፤ ብዙ ጀማሪ ምሩቃንና ሰልጣኞች ሊሳተፉበት የሚገባ ምቹ ዘርፍ ነዉ፡፡

ለዚህም፤ የቋንቋ ችሎታን የማሻሻል፤ የዲጂታል አሠራር ሥርዓትን የመፍጠር፤ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን መረጃ በማልማትና በማዘመን፤ አለፍ ብሎም በትብብርና በትስስር መጠነኛ ልማት በማከናወን የቱሪዝም ግብይት ተዋናይ መሆን፤ ከብዙ በጥቂቱ እንደዕድሎች ሊታዩት ይገባል፡፡

በመሆኑም፤ ዉድ ምሩቃንና ሰልጣኞች፡-

ወደዕዉቀት-መር ማህበረሰብና ፖሊቲካል-ኢኮኖሚ እየገሰገሰች ያለች ኢትዮጵያ እንደእናንተ ያሉ የዕዉቀት፤ የክህሎትና የጥበብ አርበኞችን በእጅጉ ትሻለች፡፡

በተለይም፤ የኢትጵያንና የሕዝባችንን አንድነት በማጠናከር፤ ሉዓላዊነታችንን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልገዉን ጠንካራና የማይበገር ፖሊቲካል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ለማፋጠን፤ ሚናችሁ እጅግ የላቀ በመሆኑ፤ በትጋት እንድትሰሩ አደራ እላለሁ፡፡

በመጨረሻም፤ የምሩቃንና የሰልጣኝ ጥራት ባለቤቶች መምህራኖችና አሰልጣኞች በመሆናቸዉ፤ በ2013 ትምህርትና ሥልጠና ዘመን የላቀ ምርምርና የማስተማር ሥራችሁን በማበርከታቸዉ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኛችሁት ምሁራን፤ እናንተም የልፋታችሁን ፍሬ በማግኘታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፤ በተገኘዉ ተጨማሪ ድልና አቅም ኢትዮጵያን በተሻለ መነሳሳት እንድታገለግሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በዕዉቀት፤ ክህሎትና ስብዕና የተገነባ ዜጋ በማፍራት፤ ወደዕዉቀት-መር ማህበረሰብና ወደማይበገር ፖሊቲካል ኢኮኖሚ በሚደረግ ሽግግር ድርሻችንን የጎላ እናድርግ!