የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን ልኬትና የጨቅላ ህፃናት ኤች አይ ቪ ምርመራ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን ልኬትና የጨቅላ ህፃናት ኤች አይ ቪ ምርመራ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ ።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የፕሮግራሞች ዘርፍ ፅህፈት ቤት ኃለፊና አማካሪ አቶ ፍቃዱ ያደታ፥ ኤች አይ ቪ ኤድስ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከታወቀበት ጀምሮ ስርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት አመታት በተደረጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት በሀገራችን ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ የመያዝ ምጣኔ በፈረንጆቹ በ2010 ከነበረው 46 በመቶ በኤድስ ምክንያት የሚከሰት የሞት መጠን 52 በመቶ የቀነሰ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡

የኤች አይቪ ቫይረስ መጠን ልኬት/ቫይራል ሎድ/ ምርመራ ሽፋንን ለመጨመርና የአገልግሎቱን ጥራት ለማሻሻል ለባለሙያዎች አቅም መገንባታ እንዲሁም የታካሚዎች ግንዛቤ ማሳደግ ትኩረት የሚሹ   ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ስራዎች ማጠናከር እንደሚገባም ነው የገለፁት፡፡

የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት በቦታ፣ በተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች፣ በፆታ እንዲሁም በገጠርና በከተማ የሚለያይ ሲሆን÷ በከተሞች የሚታየው የሥርጭት ምጣኔ በገጠር ካለው በ7 እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑም በውይይቱ ተገልጿል፡፡

ውይይቱ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፥ በ2013 ዓ.ም በአገልግሎቱ ዙሪያ የታዩ ዋና ዋና ማነቆዎችን መለየትና በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸው ተግባራት ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ እንደሚጠበቅ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።