በሰላም ኖቤል ሽልማት አገር እንዲሸጥላቸው የሚሹ ብልጣብልጦ

በነስረዲን ኑሩ
ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን ይፋ ባደረጉ ቅጽበት የውጭ መገናኛ ብዙኃን የዜና ርዕስ ተመሳሳይና አስገራሚ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር በመዝመት ኢትዮጵያን የሰላም አማራጮችን ሁሉ አሻፈረኝ ብሎ ጦርነት ከከፈተው አሸባሪው እና ወራሪው ቡድን ለማጽዳት የተጀመረውን ዘመቻ ከፊት ሆነው ለመምራት መወሰናቸው አገርን የመታደግ ግዴታ እንዳለበት መሪ ሊያስመሰግናቸው ሲገባ ፅንፍ ከያዙ የውጭ መገናኛ ብዙኃን በኩል የጎረፈው ግን የትችት ናዳ ነበር፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ ላይ የሃሰተኛ ዘገባዎችን በመስራት ተጠምደው የቆዩት ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ሮይተርስ፣ ቢቢሲ እና ሌሎችም የየትኛውም ሃገር መሪ ሊያደርገው ቀርቶ ሊያስበው የማይፈልገውን ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድንቅ ውሳኔ የዘገቡበት መንገድ ለሌላ ተጨማሪ ትችትና ትዝብት ዳርጓቸዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት መገናኛ ብዙኃን በተመሳሳይ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ (የይዘት ሥራ መመሪያ) የሚመሩ ይመስል ጉዳዩን የዘገቡበት መንገድ ፍጹም ተመሳሳይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ለማሳነስ የደከሙበትም ነው፡፡
ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ እና ሮይተርስ በፊትለፊት ገጾቻቸው “የአለም የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጦር ሜዳ ግንባር በመገኘት ጦርነትን ከፊት ለፊት ሆኜ እመራለሁ አሉ” ሲሉ ነበር የዘገቡት፡፡
አሁናዊው እና ትኩሱ ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእዘምታለሁ ውሳኔ ቢሆንም እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ግን በአርዕስቶቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሁለት ዓመት በፊት ስላሸነፉት የሰላም ኖቤል ሽልማት ማንሳታቸው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ አሸባሪው እና ወራሪው የሕወሓት ቡድን በንጹሃን ላይ እየፈጸመ ለሚገኘው ግፍ በአጭር ጊዜ መቋጫ ለማበጀት፤በዚያውም በእነ አሜሪካ እና አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ኢትዮጵያ ላይ የታቀደውን ዘመናዊ ቅኝ ገዥነት ህልም እንደማይሳካ ግልፅ ለማድረግ ነው፡፡
የሰላም ኖቤል ሽልማቱም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡበት ጥቂት ወራት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በመላው አፍሪካ ስለሰላም በተጓዙት ርቀት እና ባመጡት የሚታይ ለውጥ የተነሳ የወሰዱት እንጂ ከማንም የተበረከተላቸው ገጸ በረከት አለመሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡፡
በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ኖቤል ሽልማቱ ለእኔ ነበር የሚገባው ሲሉ መናገራቸው በርካቶችን ፈገግ አስደርጎ ማለፉ የቅርብ ክስተት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በወቅቱ ትራምፕ በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እንደይቀሰቀስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቴ ለአሸናፊነት ያበቃኛል ማለታቸው፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ሳትፈልግ የገባችበት ጦርነት መች እና በእነማን እንደተጠነሰሰ የሚያመላተው ነገር ይኖራል፡፡
የሰላም ኖቤል ሽልማት በእርግጥ ስለሰላም ለደከመና ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከተ ግለሰብ የሚበረከት እንደመሆኑ የወቅቱ ኖቤልም ለተገቢው ሰው መበርከቱን አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብዥታ ለነበረባቸው አካላት በተግባር እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡
የሚመሯት አገር በውስጥ ባንዳና በውጭ ባዳ ሰላሟ ሲደፈርስ፣ ዜጎቿ ላይ ለመስማት የሚቀፍ ግፍና በደል ሲፈጸም በቤተ መንግሥቴ ቁጭ ብዬ ማየት አልችልም፤ ንጹኃን ዜጎች መሞት፣ መፈናቀል እና መራብ አይገባቸውም፤ ሴቶች፣ እናቶች እና ልጃገረዶች እንስሳዊ አስተሳሰብ ባላቸው የሽብር ቡድን አባላት አይደፈሩም በሚል ቁጭት አንድ ህይወታቸውን ይዘው እሳት ከሚዘንብበት ግንባር መገኘታቸው ብቻ ለተጨማሪ የኖቤል ሽልማት የሚያሳጫቸው ቢሆን እንጂ አያስወቅሳቸውም፡፡
የዓለም ታሪክ በደማቁ የሚመዘግበውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኑ እነ ሲኤንኤን የቱንም ያህል ለማሳነስ ቢጥሩም እንደ ቱኒዚያዊው ጋዜጠኛ ሳሊህ አልአዝረቅ አይነቶቹ እልፍ ጋዜጠኞችና የእውነት አጋሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ለሌሎች መሪዎች ማስተማሪያነት እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡
ጋዜጠኛ ሳሊህ አልአዝረቅ በአል ሂዋር ቴሌቪዥን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የወታደር ዩኒፎርም ለብሶ አማፂዎችን ፊትለፊት እየተዋጋ ነው ምናልባት ይህ ክስተት ለኛ ለአረቦች አዲስ ሊሆን ይችላል፤ በኢትዮጵያውያን ግን የተለመደ ነው፤ ጀግንነት ደግሞ የራሳቸው ነው ሲል ነው ከእውነት ጎን የቆመው።
የትኛው የአረብ መንግስት ወይም የፓርላማ አባል ወይም ባለሀብት ነው ለአገሩ ሲል ሥልጣኑን ጥሎ ሊዋጋ ጫካ የወረደው? በማለትም ማንም የለም! ሲል ራሱ ይመልሳል፡፡
የሆነው ሆኖ የሰላም ኖቤል ሽልማት ለአገር መሪ ሲሰጥ በማግስቱ አገሩን የሚበትን ጦርነት ቢከፈትበት እኔ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ነኝ ብሎ ቁጭ ይበል፤ አገሩንም ለወራሪና ባንዳ አሳልፎ ይስጥ የሚል ሕግም የሞራል ልዕልናም የለም፤ ይልቁንም አገሩን ወደ ሰላም ለመመለስ እንዲዋደቅ ተጨማሪ ስንቅ ይሆነዋል እንጂ፡፡