በጦርነትና ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ አጭር የፅሑፍ መልዕክት መላኪያ ይፋ ሆነ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በጦርነትና ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆን 9400 አጭር የፅሑፍ መልዕክት መላኪያ ይፋ አደረጉ።
የአጭር የፅሑፍ መልዕክት የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሩ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ነው።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የበላይ ጠባቂና የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ “እኔም ለወገኔ” በሚል መሪ ቃል በጦርነትና ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብርን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በድርቅና ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖች በተለይም ሴቶች፣ ህጻናት እና አረጋዊያን ለከፋ ሰብዓዊ ችግር መጋለጣቸው ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተጎጂ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ ሰብዓዊ ድጋፉን “እኔም ለወገኔ” በሚል መሪ ቃል አጠናክሮ ለመቀጠል አስቸኳይ የልገሳ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በመተግበር ላይ መሆኑንም ገልጿል።
በዛሬው ዕለትም የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአጭር የፅሑፍ መልዕክት ድጋፍ ማሰባሰብ የሚያስችለውን 9400 ይፋ አድርገዋል።
በዚህም ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖች ወደ 9400 “OK” ብለው በመላክ ከአንድ ብር ጀምሮ መለገስ እንደሚችሉ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡