ኢትዮጵያ ዘመናዊ የላይዳር ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑ ተነገረ

መጋቢት 2/2014 (ዋልታ) በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ዘመናዊ የአየር ላይ ቅየሳ ሥራዎች የመስክ ምልከታ በአዲስ አበባ አየር ክልል ላይ አድርገዋል።
የላይዳር ቴክኖሎጂ ከአየር ላይ በመሆን በየሴኮንዶች ከፍተኛ ጉልበት ያለው የሌዘር ጨረር በመልቀቅ ምድር ላይ ያሉ ቁሶችን ከፍታ ሞዴል የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ነው።
ኢንስቲትዩቱ ዓለም ዐቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የጂኦስፓሻል መረጃ መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለተልዕኮው መሳካት ያደረገው ዝግጁነት የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ የሚያመርታቸው መረጃዎች ለአገር ዕድገት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተቋሙ ዘርፈ ብዙ ስምሪት ስላለው ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እቅዳቸውን ለማሳካት የጂኦስፓሻል መረጃን በግብዓትነት የሚጠቀሙ እንደ መሬት አስተዳደር፣ የመንገድ እና ግድብ ግንባታ፣ የመስኖና ተፋሰስ ልማት፣ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እና የመሳሰሉ ቁልፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከዚህ ተቋም አገልግሎቱን ማግኘት አለባቸው ብለዋል።
የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ቱሉ በሻ (ዶ/ር) ዘርፉ ለአገሪቱ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ መሳካት ጉልህ ሚና ስላለው ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር በመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ኢትዮጵያ ወደ ሥራ ያስገባችው የአየር ላይ ቅየሳ ላይዳር ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ ቴክኖሎጂውን ከሚጠቀሙ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።
ዘመናዊ በአየር ላይ የመሬት ካርታ ቅየሳ ቴክኖሎጂ ለመሥራት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሊሠራ ለታሰበው ከእንጦጦ ወደ ኮተቤ የሚሄድ መንገድ የከፍታ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ሂደት ሚኒስትሩን ጨምሮ የልዑክ ቡድኑ ከበረራና ከአየር ካርታ ቅየሳ ባለሙያዎች ጋር በበረራው ተሳትፈዋል፡፡