አሸባሪው ሸኔንና ሌሎች የጥፋት ኃይሎችን በፅናት እንታገላለን – የምስራቅ ሀረርጌ ወጣቶች

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ አሸባሪው ሸኔንና ሌሎች የጥፋት ኃይሎችን በፅናት እንታገላለን ሲሉ የምስራቅ ሀረርጌ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ‘’የኛ ዘመን ወጣቶች ሚና’’ በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ ፈተናዎችን መሻገር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ተወያይቷል።

ዋልታ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የሀገሪቱ ሰላም እንዲጎለብት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝነት በመቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።

አሸባሪው ሸኔ እና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች ሀገርን ማተራመስ አላማ አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰው ወጣቶች አንድነታቸውን በማጠናከር የሽብር ቡድኖቹን እኩይ አላማና ተግባር ማክሸፍ ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አንፃርም በመደራጀትና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም እያከናወኑት የሚገኘው ተግባር በማጠናከር ሰላምን ለማስፈንና የሽብር ቡድኖችን ለመታገል በትኩረት እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

የተለያዩ አጀንዳችን ቀርፀው ሀገሪቱን ለመበታተን እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ቡድኖችንና ፖለቲከኞችን አላማ በአግባቡ መረዳትና መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቶች በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ እና አዲስ ስርዓት እንዲገነባ እንዳስቻለ ሁሉ አሁንም አሸባሪዎችን በመታገል የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት እንዲጎለብት እና የሀገሪቱ ሰላም እንዲጠናከር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)