ጤና ደጉ-ኩፍኝ


#ጤና_ደጉ

ኩፍኝ (Measles) በፍጥነት ተላላፊ የሆነ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ቫይረሱ በበሽታው በተያዘ ሰው አፍንጫ እና ጉሮሮ ውስጥ በሚገኝ ንፍጥና ፈሳሽ ውስጥ ይኖራል። ቫይረሱ በምናስልበትና በምናስነጥስበት ወቅት በቅርብ ወዳለ ሰው ሊተላለፍ ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ በበሽታው የተያዘ ሰው ባለበት ክፍል ውስጥ ቫይረሱ እስከ ሁለት ሰዓት የሚቆይ ሲሆን በንጣፍና ወለል ላይም ሊገኝ ይችላል። ሰዎች በቫይረሱ የተበከለውን አየር በመተንፈስ ወይም የተበከለውን ገጽ በመንካት ከዚያም አይናቸውን፣ አፍንጫቸውን ወይም አፋቸውን በመንካት በኩፍኝ ሊያዙ ይችላሉ።

የኩፍኝ በሽታ በተለይ በህጻናት፣ እርጉዝ ሴቶች እና በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎች ላይ ከባድ ችግርን ያስከትላል።

በሽታው በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየተስፋፋ መሆኑንና በየዓመቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ እያሳዬ እንደሆነ ይነገራል። ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ፣ ዓመታዊው የኩፍኝ በሽተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡

የበሽታውን ምልክቶች፣ ስርጭቱን እና መከላከያ ዘዴውን ጨምሮ የኩፍኝን መሰረታዊ ነገሮች መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡

የበሽታው ምልክቶች፡-

የኩፍኝ ምልክቶችን ማወቅ አስቀድሞ አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን ለማድረግና ፈጣን ህክምና ለመስጠት ወሳኝ ነው። ምልክቶቹም፡-

• ከፍተኛ ትኩሳት
• ሳል
• የአፍንጫ ፍሳሽ መኖር
• የዓይን መቅላት እና
• በሰውነት ላይ ሽፍታ መውጣት
• በአፍ ውስጥ የሚወጡ ዕብጠቶች ጫፍ ላይ ሰማያዊ ወይም ነጭ ቀለም መፈጠር እና
• ከፊት በመጀመር ወደቀሪው የሰውነት ክፍል የሚተላለፍ ሽፍታ ነው።

መተላለፊያ መንገዱ፡-

ኩፍኝ በማሳል እና በማስነጠስ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ይተላለፋል። የተበከሉ ቦታዎችን በመንካት ሊሰራጭ ይችላል፡፡

የክትባቱ አስፈላጊነት፡-

ኩፍኝን ለመከላከል በጣም ውጤታማው መንገድ የኩፍኝ ክትባት መከተብ ነው። ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ልጆቻቸው የኩፍኝ ክትባቱን የጤና ተቋማት በሚያወጡት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መከተብ አለባቸው።

ሕክምናው፡-

የኩፍኝ በሽታን ለይቶ ለማከም የሚያስችል የተለየ የፀረ-ቫይረስ ሕክምና የለውም። ነገር ግን ድጋፍ ሰጪ እንክብካቤ ይኖሩታል፡፡ ምልክቶችን ለመቆጣጠር እና ተያያዥ ውስብስብ ችግሮችን ለመከላከል የሚረዳ ሕክምና ነው ሊሰጥ የሚችለው። በዚህም ቫይታሚን ኤ፣ አንቲባዮቲክስ እና ኢሚኖገሎቡለን… ወዘተ በብዛት በሀኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶች ናቸው።

በኩፍኝ በሽታ የተጠረጠሩ ሰዎች ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለባቸው፡፡ የኩፍኝ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ሁሉም ሕብረተሰብ ክትባት መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

ምንጭ፡-
ሀኪም ገፅ
የዓለም ጤና ድርጅት
ሲ.ዲ.ሲ
ኒው ሜዲካል ኔት

በቴዎድሮስ ሳህለ