ከተሞቻችን – ነቀምቴ

ነቀምቴ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና መቀመጫ ሆና በማገልገል ላይ የምትገኝ ለምለሟ የንግድ ከተማ ናት፡፡ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ በ328 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ በ1830 ዓ.ም በደጅ አዝማች ሞሮዳ በከሬ እንደተቆረቆረችም ይነገርላታል።

ደጋማ የአየር ንብረት ያላት የነቀምቴ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 88 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ኮረብታማ እና ሜዳማ መልክዓ ምድራዊ ተፈጥሮንም ተላብሳለች።

የምዕራብ ኦሮሚያ ትልቋ ከተማ እንደሆነች የሚነገርላት ነቀምቴ አራት የመውጫ መግቢያ በሮች አሏት፡፡ እነዚህም በሮች ከተማዋን ከአዲስ አበባ፣ ከጅማ፣ ከአሶሳ እና ከባሕርዳር ጋር ያገናኛሉ።

በሰባት ክፍለ ከተሞች የተዋቀረችው ነቀምቴ በከተማዋ ብዙ የሰፈር ስያሜዎች አሏት፡፡ ከእነዚህም በኪጃማ፣ ቀሶ፣ ቦርድ፣ ሸዋበር፣ አጂፕ፣ ማሪያም እና ደርጌ ጥቂቶቹ ናቸው።

በ1881 ዓ.ም እንደተገነባ የሚነገርለት የንጉስ ኩምሳ ሞሮዳ ቤተ-መንግስትን ጨምሮ ጥንታዊቷ የማሪያም ቤተ ክርስቲያን፣ ሶርጋ ሰው ሰራሽ ሀይቅ እና ወለጋ ሙዚየም በከተማዋ ካሉ የቱሪስት መስህቦች መሀል ተጠቃሾች ናቸው።

በዙሪያዋ በሚገኘው እምነበረድ፣ ወርቅ እና ቡና ምርት የምትታወቀው ነቀምቴ በጥራቱ በገበያ ላይ ተፈላጊ የሆነው የወለጋ የቅቤ ምርት በሰፊው የሚገኝባት ከተማም ናት።

በከተማዋ ቢቂልቱ ለካ 1ኛ ደረጃ፣ ኢፋ ቦሩ፣ ቢፍቱ ነቀምት 2ኛ ደረጃ፣ ካቶሊክ ኪዳነምህረት የሚሰኙ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ፣ ዳንዲ ቦሩ ኮሌጅ፣ ሪፍት ቫሊ እንዲሁም የወለጋ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎች ይገኛሉ።

የወለጋ ተወዳጅ ባህላዊ ምግቦች የሆኑት አንጮቴ፣ መሮ፣ ጨጨብሳ እና ጩምቦ በነቀምቴ ከተማ የሚዘወተሩ ሲሆን “ቡነ ቀላ” ወይም ቡና በቅቤ የማህበረሰቡ መገለጫ የሆነ መጠጥ ነው።

ነቀምቴ ለመጀመሪያ ጊዜ መፅሀፍ ቅዱስን ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ የተረጎመው “ኦነሲሞስ ነሲብ” የቀብር ስፍራ መገኛ ከመሆኗም ባሻገር የተለያዩ የጥበብ ሰዎች የትውልድ ስፍራም ነች።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትውስታችሁን አጋሩን።

መልካም ሳምንት!!

በአዲስዓለም ግደይ