“ሀረ ሸይጣን ሀይቅ” – አስደናቂው የተፈጥሮ መስህብ


ሀረ ሸይጣን ሀይቅ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ከሚገኙ ከተፈጥሮ የመስህብ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሀይቁ ከዞኑ ከተማ ወራቤ በስተሰሜን አቅጣጫ በ31 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በስልጢ ወረዳ በአጎዴ ሎብሬራ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል። ከአዲስ አበባ ወደ ሀይቁ ለመድረስ ደግሞ 174 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ።

ሀረ ሸይጣን ሀይቅ ከስያሜው ጀምሮ ካረፈበት የመሬት ገጽታና በየሰዓቱ ከሚታየው የውሃው መልክ መቀያየር የጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛትና በማስደነቅ የሚታወቅ ነው።

የሀይቁ ስያሜ በአፈ ታሪክ “ሀርበር ሼጣን” ወይም “ዞር በል ሰይጣን” ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ “ጎርፍ አዘል ሰይጣን” በማለት እንደተገለጸ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የሀይቁ የውሃ መልክ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ቀለማትን መልክ ይይዛል። ሰማያዊ፣ አረንጓዴ፣ እና ቀይ ቀለማትን መልክ ሲይዝም ይስተዋላል።

የሀይቁ ቀለም ወደ ተለያዩ ቀለማት መልክ የሚቀያይረው በዙሪያው የሚገኘው ተፈጥሮ ከፀሃይ ብርሃን ጋር በሚያደርገው መንፀባረቅ መሆኑን እና ሐይቁ በተፈጥሮ የሚቀያይረው ሂደት እንደሌለም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ታዲያ ይህ አስደማሚው ሀይቅ ፀሀይ አቅጣጫዋን በምትቀያየርበት ጊዜ የሀይቁ መልክ በአከባቢው የሚገኙትን ደን፣ ዕጸዋት፣ እና ሌሎች የተፈጥሮ መልኮችን በማንፀባረቅ የተለያዩ ቀለማትን መልክ ይይዛል። ይህ የውሃ መልክ መለዋወጥ ደግሞ ለሀይቁ ድንቅ ውበትን አላብሶታል።

ሀይቁ ከመሬት ንጣፍ በታች የሚገኝ ሲሆን አቀማመጡ ክብ እና የጎድጓዳ ሰሃን ቅርጽ የያዘ ነው። የጎን ስፋቱ 2 ሺሕ 400 ሜትር እንደሚደርስ እና ጥልቀቱ እንደማይታወቅ ነው የተለያዩ መረጃዎች የሚያሳዩት።

የአከባቢው ነዋሪዎችንም ሆነ ሀይቁን ሊጎበኙ የሚመጡ ጎብኚዎችን ከሚያስደንቃቸው ነገሮች አንዱ በሀይቁ የዳገት አፋፍ ላይ ሆነው የሚወረውሩት የድንጋይ ጠጠር ወደ ውሃው መድረስ አለመቻሉ ነው። በዚህም ወደ ሀይቁ ድንጋይ የሚወረወር ሰው ድንጋይ መወርወሩን እንጂ የተወረወረው ድንጋይ ወደ ሀይቁ መድረሱን ማረጋገጥ አይችልም፡፡

ሀይቁ ዙሪያውን ክብ ሲሆን ጥልቀቱ ከፍተኛ እንደሆነም ይነገራል፡፡ የሀይቁ ዙሪያ በተፈጥሮ የሀገር በቀል ዛፎች እና ሰው ሰው ሰራሽ ደን የተከበበ ነው፡፡ በአእዋፋት ዝማሬ ታጅበው ተዳፋታማውን ተፈጥሮ እየቃኙ ወደ ሀይቁ ለመድረስ የቁልቁለት መንገዶችን መጓዝን ይጠይቃል፡፡ በሀይቁ ዙሪያ የሚቃኙት የመልክአ ምድር አቀማመጥ ከተፈጥሮ ጸጋዎች ጋር አከባቢው ልብን ይማርካል፡፡ ወደ ሀይቁ ዳርቻ ሲደርሱም ነፋሻማነቱ ነፍስን ያድሳል፡፡

የስልጤ ዞን ሀረ ሸይጣን ሀይቅን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህብ በለቤት ሲሆን የአይናጌ ዋሻ፣ የሙጎ ተራራ፣ የጊስት ጣሂራት ጥንታዊ መስጂድ፣ የአልከሶ መስጊድ፣ የአሳኖ ትክል ድንጋይ፣ የአሹቴ ፍል ውሃ፣ አባያ/ጡፋ/ ሐይቅ እንዲሁ ዋሻዎችና ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች ይገኛሉ፡፡

ስልጤ ዞንን ይጎብኙ አገርዎን ይወቁ!!

ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ