ከተሞቻችን – ቦንጋ

 


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እና የከፋ ዞን አስተዳደር መቀመጫ የሆነችው ቦንጋ ከተማ በ1565 ዓ.ም በጊዜው በነበሩ የከፋ ንጉስ ቦንጌ ታቶ የተመሰረተች ስትሆን ቀደምት ከሆኑ የሀገራችን የንግድ ከተሞች አንዷ ናት።

ከመዲናችን አዲስ አበባ 458 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የከተመችው ቦንጋ ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 714 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። ወይናደጋ የአየር ፀባይ እና ወጣ ገባ የሆነ የመሬት ገፅታ አላት።

የከተማዋ ስያሜ የሆነው “ቦንጋ” የሚለው ቃል “ቦንኖጌ” ከሚለው የካፊቾ ቋንቋ የተገኘ ሲሆን ይህም በሕዝቡ መካከል በደል አልያም አለመግባባት ሲፈጠር በርሳቸው (በንጉሱ) አምላክ ለማለት የሚጠቀሙበት ቃል እንደነበር ይነገራል።

በአራት ቀበሌዎች ማለትም ቦንጋ1፣ ቦንጋ2፣ ጊምቦ እና ውሽውሽ በሚል የተዋቀረችው የቦንጋ ከተማ ታዋቂ የሰፈር ስያሜዎች ያሏት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ መንቲና፣ ኬንቴሪ፣ ቡስታ፣ ኪዳነምህረት፣ አስጣጣዊ፣ ሶብራ፣ ገዳም፣ ካያ ኬላ ተጠቃሾች ናቸው።

በከተማዋ ከሚገኙ እና ተጠቃሽ ከሆኑ የትምህርት ተቋማት መካከል ግራዝማች ጳውሎስ፣ ቢሻው ወልደ ዮሀንስ፣ ባርታ፣ ሸታ እና ሌሎች የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ጨምሮ የቦንጋ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና ቦንጋ ዩኒቨርስቲ ይገኙበታል።

ቦንጋ የከፊቾ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው “ማሽቃሬ ባሮ” በድምቀት የሚከበርባት ከተማ ስትሆን ይህም አዝመራን መሰረት አድርጎ ዘመንን በመቁጠር የሚከበር ነው። በዓሉ የተማፅኖ፣ የእርቅ እና አመታዊ የስራ ግምገማ ስርዓትን ያካተተ ነው።

ጉርጉቶ (የእግዜር ድልድይ) ከቦንጋ ከተማ በ10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ድንቅ ተፈጥሯዊ መስዕብ ሲሆን በተጨማሪም ከ100 ሜትር በላይ ከፍታ ያለው የቦንጋ ፏፏቴ፣ ዳዲበን ፍል ውሃ እና ከአመት እስከ አመት የሚፈሱት የባርታ፣ የዲንቻ እና የሸታ ወንዞች በዙሪያዋ ይገኛሉ።

ቦንጋ “ኮፊ አረቢካን” ለዓለም ያስተዋወቀች የቡና መገኛ ምድር ከመሆኗ በተጨማሪ በቀርከሀ ምርት እና ለየት ባለ የበግ ዝርያ መገኛነቷ ትታወቃለች። በከተማዋ ዙሪያ የሚገኘው ጥቅጥቅ ደን “የካፋ ባዮስፌር ሪዘርቭ” በሚል በ2010 ዓ.ም በዩኔስኮ መዝገብ ላይ የሰፈረ ልዩ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ነው።

ቦንጋ ብዙ የሀገር ባለውለታዎችን ያፈራች ሀገር ናት። የዘመናዊ መንኩራኩር ዲዛይን ባለቤት እንዲሁም ጂፒስ እና የሚሳኤል መቃወሚያን የሰራው እና በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ጣቢያ (ናሳ) ውስጥ ሳይንቲስት የነበረው ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ ከቦንጋ ምድር የተገኘ ድንቅ የሀገር ልጅ ነው።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትውስታችሁን አጋሩን።

መልካም ሳምንት!

በአዲስዓለም ግደይ