የፌስቡክና የኢንስታግራም ልጥፎች ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ማለማመጃ ሊሆኑ ነው


ሰኔ 19/2016 (አዲስ ዋልታ) የፌስቡክና የኢንስታግራም እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ በአውሮፓ ሕብረትና በእንግሊዝ ያሉ ደንቦኞች በፌስቡክና በኢንስታግራም የሚለጥፏቸውን ይዘቶች ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ማለማመጃ አድርጎ ለመጠቀም ማቀዱ ተሰምቷል።

ከዛሬ ጀምሮ በተጠቀሱት የዓለም አካባቢዎች የኩባንያውን መተግበሪያዎች ተጠቅመው የሚለጥፏቸውን ማንኛውንም ይዘቶች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴል ለማሰልጠን ሊጠቀም መሆኑ ነው የተገለጸው።

ሆኖም በአውሮፓ ከዚህ ጋር በተያያዘ 11 ክሶች እንደቀረቡበትና በአይሪሽ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን ጥያቄ ዕቅዱ እንዲዘገይ ተድርጓል።

የሜታ ኃላፊዎች በውሳኔው ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጸው ለተጠቃሚዎቻችን አካባቢያቸውን የሚወክል ትክክለኛ መረጃ ለማቅረብ አስቸጋሪ ይሆንብናል ሲሉ ገልጸዋል።

ሜታ ኩባንያ ከአውሮፓ ሕብረት መረጃ ወስደው ሲጠቀሙ የነበሩትን የጎግልና የ”ኦፕን ኤ.አይን ፈለግ” ተከትሎ ነው እየሰራ ያለው ብለዋል።

በአውሮፓ ሕብረትና እንግሊዝ ያሉ ተጠቃሚዎች በጥብቅ የመረጃ ጥበቃ ህግ ከለላ የሚደረግላቸው በመሆናቸው ሜታ መረጃቸውን እንዲጠቀምበት ፈቃደኝነታቸውን ሲጠይቅ መቃወም ይችላሉ ተብሏል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት የማስተማሩ ተግባር ሲጀመር ተጠቃሚዎች ድርጅቱ ስለሚያስተዋውቃቸው የአሰራር ለውጦች በማስታወቂያ ወይም በኢሜይል እንዲያውቁት እንደሚደረግም ተነግሯል።

ተጠቃሚዎች ኩባንያው መረጃቸውን እንዲጠቀምበት መስማማት ወይም አለመስማማት ይችላሉ ተብሏል።

ኩባንያው ተጠቃሚዎች መረጃቸውን እንዳይጠቀም የሚቃወሙ ከሆነ በፅሁፍ ማብራሪያ እንዲሰጡ የሚያስችል ፎርም አዘጋጅቷል። ማብራሪያቸውን ከተገቢው የመረጃ ህግ ጋር በማስተያዬት እንደሚያየው አስታውቋል።

በአሜሪካና በሌላው የዓለም ክፍል ያሉ የሜታ ተጠቃሚዎች መረጃቸውን ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ማስተማሪያነት የመዋሉን ነገር የውዴታ ግዴታ ነው ሲል ስካይ ኒውስ ዘግቧል።