የውሃ ወለድ በሽታዎች እና ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች

#ጤና_ደጉ

የውሃ ወለድ በሽታ በተበከለ ውሃ አማካኝነት የሚከሰቱ ህመሞችን ያጠቃልላል፡፡ የበሽታው መንስኤ በረቂቅ ተሕዋስያን የሚመጣ ሲሆን በቫይረስ፣ ባክቴሪያ እና ፕሮቶዞዋ ወይም በጥገኛ ተውሳኮች የተበከሉ ምግቦችን በመመገብና እና መጠጦችን በመጠጣት የሚመጣ ነው።

የመጠጥ ውሃ መገኛዎች ማለትም ምንጮች፣ ኩሬዎች፣ ወንዞች እና ሀይቆች እንዲሁም የውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች በእነዚህ ረቂቅ ተህዋሲያን ሲበከሉና ሰዎች የተበከለውን ውሃ ሲጠጡ ወይም በውሃው የተዘጋጁ ምግቦችን ሲመገቡ በሽታው በቀላሉ ይይዛቸዋል። የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉድለቶች ችግሩን የበለጠ ያባብሱታል።

በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ውሃ ወለድ በሽታዎች

ከተለመዱ ውሃ ወለድ በሽታዎች ውስጥ ጃርዲያ፣ ተቅማጥ፣ ታይፎይድ፣ ሄፐታይተስ ኤ እና ኢ፣ ኮሌራ፣ ኢ.ኮላይ፣ የጊኒ ዎርም እና ሌሎች ጥገኛ ትላትሎች ተጠቃሽ ናቸው።

ለውሃ ወለድ በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች፡-

• የንጹህ ውሃ እጥረት
• ደካማ የንፅህና አጠባበቅ
• ተገቢ የፍሳሽ ማስወገጃዎች አለመኖር እና የቆሻሻ አወጋገድ ችግር
• የተጨናነቀ የመኖሪያ አካባቢ
• በተፈጥሮ አደጋዎች – በአደጋ ምክንያት የተበላሹ የውኃ አካላት ለብክለት መንስኤ እንደሆኑ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የውሃ ወለድ በሽታ የመከላከያ ዘዴዎች፡-

• የውሃ ወለድ በሽታን ለመከላከል የግል እና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፣ የመጠጥ ውሃን ንፅህና መጠበቅና የምንመገበውን ምግብ እንዲሁም የመመገቢያ ዕቃዎችን በጥንቃቄ መያዝ ተገቢ ነው።

• ምግብ ከመመገባችንም ሆነ ከተመገብን በኋላ፣ ምግብ ከማብሰላችን በፊት እንዲሁም ከመጸዳጃ ቤት ስንመለስ እጃችንን በሳሙና መታጠብ

• የምግብ ማብሰያና መመገቢያ ዕቃዎችን ማጠብ እና በንጹህ ቦታ ማስቀመጥ

• ጥሬ ወይም ያልበሰሉ አትክልትና፣ ከባህር የሚገኙ ምግቦችን አብስሎ መመገብ ካልሆነም ከመመገብ መቆጠብ ከውሃ ወለድ በሽታዎች ለመከላከል ያግዛል።

• መጸዳጃ ቤት መጠቀም፣ አካባቢን ማፅዳትና ቆሻሻን በተገቢው መንገድ ማስወገድ በአካባቢ ያለን የውሃ አካል እንዳይበክል ማድረግ

• የውሃ ማጣሪያ መሳሪያዎችንና የውሃ ማከሚያ ኪኒኖችን መጠቀም እንዲሁም ውሃን አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠጣትም ውሃውን ደህንነት ለማረጋገጥ ይረዳል።

• ከዚህ በተጨማሪ የውሃ መገኛ ምንጮችን ብክለት ለመከላከል ተገቢውን የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልጋል።

• እንደ ሄፕታይተስ ኤ እና ታይፎይድ የመሳሰሉ በሽታዎች ክትባት ስላላቸው ወቅቱን ጠብቆ መከተብ ይመከራል፡፡ ጤና ይስጥልን!!

በቴዎድሮስ ሳህለ