የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ታንዛንያ አመራ

ነሐሴ 27/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ የወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ ወደ ታንዛንያ አቅንቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከታንዛንያና ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የሚጫወት ሲሆን ከነሐሴ 12/2016 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ታንዛንያ ከማምራቱ አስቀድሞ የሀገር ቤት የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም አከናውኗል።

ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከታንዛንያ ጋር ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም ዳሬ ሰላም ላይ ያካሂዳል።

ሁለተኛና የሜዳ ጨዋታውን ጳጉሜ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ዳሬ ሰላም በሚገኘውና የታንዛንያ ብሔራዊ ስታዲየም በሆነው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም እንደሚያደርግም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል። 24 ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ ይካሄዳል፡፡