መስከረም 30/2017 (አዲስ ዋልታ) ቡና የኢኮኖሚያችን ዋልታ ነው፤ በቡና ልማት ያሳየነው የእድገት ርምጃም ይህንኑ ያንፀባረቀ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
“እጅግ አስደናቂ የሆነውን አንድ ሚሊዮን ቶን ቡና የማምረት ግባችንን መትተናል። የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚነትም ትርጉም ባለው መልክ እድገት አሳይቷል” ሲሉም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ከተግዳሮቶቻችን ባሻገር በቡና ልማት ዘርፍ የበለጠ ስኬታማ መሆናችንን ቀጥለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ይህን ቁልፍ ኢንደስትሪ የበለጠ ለማሳደግ የየድርሻቸውን እንዲወጡ እጠይቃለሁ ብለዋል።
ባለፉት ስድስት አመታት ለእድገቱ ያለንን ቁርጠኝነት በሚያሳይ ሁኔታ 8.5 ቢሊዮን የቡና ችግኞችን ተክለናል ሲሉ ገልጸዋል።
“ለቡና የእሴት ሰንሰለት የተሳለጠ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ወሳኝ ሲሆን እሴት የመጨመር ተግባርም ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫችን ነው። በቀጣይም በጠንካራ ስራ እና ፈጠራ ፀንተን ስኬቶቻችንን ማስቀጠል እና ማስፋት ይኖርብናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።