በኡጋንዳ ሉቡ መንደር ያሉ ነዋሪዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ዓይነ ስውራን አልያም የማየት አቅም የደከመባቸው ሰዎች ናቸው።
ገና ወደ መንደሩ ሲገቡ “እንኳን ወደ ሉቡ የዓይነ ስውራን ማህበር በደህና መጣችሁ የሚል ቤተሰባዊነት እንዲሰማ የሚያደርግ ምልክት ይታያል፡፡
ይህንን የዓይነ ስውራን መንደር ያቋቋምነው ዓይነ ስውር የሆኑ ሰዎች ከሌሎች የተገለሉ መሆናቸውን ከተረዳን በኋላ ነው ይላሉ የመንደሩ መሪ።
ዛሬ ላይ እነዚህ በጋራ የሚኖሩ ዓይነ ስውራን በየሳምንቱ በዕለተ ሰኞ ስብሰባ በማድረግ እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ ልጆቻቸው ትምህርት እንዲያገኙ እና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲሟላላቸው በመወያየት እየተጋገዙ ይኖራሉ፡፡
ሉቡ በፈረንጆቹ 2000 መጀመሪያ ላይ በወንዝ ዓይነ ስውርነት ወረርሽኝ (river blindness epidemic) ለተጠቁ ህጻናት እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር የተመሰረተው፡፡
በሽታው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ትምህርት ቤቱ ቢዘጋም ብዙዎች ግን እዛው መቆየትን መርጠዋል፡፡ በትራኮማ፣ በዓይን ሞራ ግርዶሽ እና በተለያዩ ምክንያቶች የማየት ችሎታቸውን ያጡ ሰዎች መንደሩን የጋራ መኖሪያቸው አደረጉት፡፡
“በመጀመሪያ ዓይነ ስውር ሲሆን ሕይወቴ በጣም ተመሰቃቅሎ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ከአዕምሮ ጤና ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥሙኝ ነበር ምክንያቱም ይህ የእኔ ፍጻሜ ነው ብዬ አስብ ስለነበር በዙሪያዬ ያሉ ጓደኞቼን ላጣ ነው በሚል ፍርሀት እጨነቅ ነበር፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንኳን አላውቅም ነበር” ይላል የመንደሩ መሪ ሞሰስ ሙጋቤ ዛሬ ላይ ያን ጊዜ ሲያስታውሰው፡፡
ሞሰስ እና ጎረቤቶቹ ማየት በሚችሉ ወጣቶች ደጋፍ እና እርዳታ ህይወታቸውን ማስተካከል እና ሁኔታዎችን መላመድ ችለዋል፡፡
ጉድለታችን ጥንካሬያችን ነው፤ እዚህ እርስ በርስ እንደጋገፋለን፤ ዓይነ ስውር ስለሆኑ ሰዎች የሚወራ አሉታዊ ነገር እዚህ ምንም ቦታ የለውም፤ እንደማንኛውም ሰው መደበኛ ሰዎች ነን ይላሉ የመንደሩ መሪ፡፡
አንደ ቢቢሲ አፍሪካ ዘገባ በኡጋንዳ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሲሆን በተለይ በገጠር አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የዓይን ህክምና የማግኘት እድላቸው አነስተኛ ነው፡፡